
ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መምሪያው የበጀት ዓመቱን የሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሥራዎች ገምግሟል። ከሩብ ዓመቱ እቅድ 68 በመቶ ማሳካት እንደቻለም መምሪያው አስታውቋል፡፡የፀጥታው ችግር በመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራው ላይ መስተጓጎል ከመፍጠሩ ባሻገር የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት ተገቢውን አውቀት እንዳይሸምቱ አድርጓል ተብሏል።
ህጻናት በትምህርት ገበታቸው ላይ ተገኝተው መደበኛ ትምህርታቸውን መከታተል ቢኖርባውም ይህንን ተግባር ተፈፃሚ ለማድረግ የሰላም መረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደደር በተገኘው አንጻራዊ ሰላም በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝገቦ እያስተማረ ይገኛል፡፡
መምሪያው ከ49 ሺህ በላይ ተማሪችን ማስተናግድ የነበረበት ቢኾንም በሩብ ዓመቱ የነበረው አፈጻጸም ዝቅተኛ እንደነበር ተገምግሟል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ያምራል ታደሰ እስካሁን ማስተማር ያልጀመሩ 15 ትምህርት ቤቶች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ በማድረግ በኩል ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ከትምህርት ቢሮ ጋር በመነጋገር የመማር ማስተማር ሥራው የተሳካ እንዲኾን የግብዓት ማሟላት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ ካሪክለም የተቀረጹ የግብረ ገብ፣ የአይ ሲቲ እና የዜግነት ትምህርት መጽሐፍትን በአጭር ጊዜ ለተማሪዎች እና ለመምህራን ለማቅርብ እየተሠራ መኾኑን ኀላፊው አስረድተዋል፡፡
በአዲስ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን በተመለከተም የመምህራን ቅጥር ተፈጻሚ እንደሚኾን መምሪያው አስታውቋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!