
ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ ክፍያ ሥርዓት (ኢ-ታክስ) የሙከራ ፕሮግራም ይፋ ተደርጓል። የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት መሐመድ የግብር አሠባሠብ ሥርዓቱን ለማዘመን የግብር ከፋዩን ማኅበረሰብ ጊዜ እና ጉልበት ለመቆጠብ እንዲሁም የግብር ስወራን ለመከላከል የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በዚህ በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስት 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በተከናወነ የቅንጅት ሥራም 12 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠብ መቻሉን ገልጸዋል።
የተሠበሠበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ያለው መኾኑን ጠቅሰው ወቅታዊ ችግሮችን በመቋቋም የተሠበሠበው ገቢ የሚያበረታታ እንደኾነ አስገንዝበዋል። ቢሮ ኀላፊው ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በባሕር ዳር ከተማ የኤሌክትሮኒክስ የግብር ክፍያ ሥርዓት በሙከራ ደረጃ ይፋ መደረጉንም ተናግረዋል። ይህም ዘመናዊ አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሠብሠብ የሚያስችል እንደኾነ ጠቅሰዋል።
የሙከራ ትግበራው ውጤታማነት ከተረጋገጠ በኋላ አርሶ አደሮችን ጨምሮ በከፍተኛ ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ዘንድ ተግባራዊ እንደሚደረግም አስታውቀዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎትን ለማሳካት በትኩረት እየሠራ ይገኛልም ብለዋል።
የቴክኖሎጅ ሽግግር እና ፈጠራ ሥራ እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ክልል ችግሮችን በመፍታት እና በማቃለል ድርሻው የጎላ በመኾኑ ተጨባጭ ለውጥ በሚያሳይ መልኩ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የኢኮኖሚ ዘርፉን ሃብት በማሠባሠብ ድልድይ ኾኖ የሚያገለግለው የገቢ ተቋም ዘመኑን የዋጀ አሠራር መከተል የግድ እንደሚለው ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በዚህ ረገድ ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ ክፍያ ሥርዓት ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የቢሮው እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መሪዎች እና ባለሙያዎች ተሳታፊ ኾነዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!