የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ስንዴን በማልማት ሂደት የሚገጥሙ ችግሮች እንደሚፈታ ተገለጸ።

38

ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ክልላዊ የማስጀመሪያ አውደ ጥናት ትናንት በባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት በአማራ ክልል ግርና ቢሮ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አግደው ሞላ ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስንዴ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መኾኑን አንስተዋል። ፕሮግራሙ ስንዴን በማምረት ሂደት ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን በትኩረት እንዲፈታ ታስቦ የተቀረፀ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር አማራ ክልልን ጨምሮ በአራት ክልሎች የሚተገበር ፕሮጀክት መኾኑን ያነሱት አስተባባሪው በአማራ ክልል ብቻ በሰባት ዞኖች በ24 ወረዳዎች በ360 ቀበሌዎች ተግባራዊ እንደሚኾን ነው ያብራሩት፡፡ ፕሮጀክቱ በክልሉ በስፋት በአሲዳማነት የተጠቃን መሬት በማከም፣ የስንዴ ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን በመፍታት፣ በገንዘብ እና ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን ለባለሙያው እና አርሶ አደሩ በመስጠት የስንዴ ልማት ሥራው ውጤታማ እንዲኾን ያግዛል ብለዋል፡፡

የአምስት ዓመታት ጊዜ ቆ,ይታ ያለው ፕሮጀክቱ 800 ሺህ በላይ ጥቂት የመሬት ይዞታ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ስለመታሰቡም ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሴት አርሶ አደሮች ላይ ትኩርት እንደሚያደርግ የገለጹት አስተባባሪው ከ800 ሺህ ተጠቃሚዎች መካከል 15 በመቶ ሴት እማወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው ያስረዱት፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ 94 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ፕሮጀክት መኾኑን ጠቁመዋል። በጀቱ የስንዴን ምርታማነትን ለመጨመር የተለያዩ ቴክኖሎጅዎችን ለመተግበር የሚውል መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ክልሉ በስንዴ ምርጥ ዘር ከፍተኛ ችግር ያለበት በመኾኑ ችግሩን በዘላቂነት ይፈታል ነው ያሉት። ምርጥ ዘር የማግኘት አቅም የሌላቸው አርሶ አደሮችን ችግር በመፍታት እንዲያለሙ ያደርጋልም ብለዋል። በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት እና ጥቁር አፈር ላይ ስንዴ ማምረት እንዲቻል በቴክኖሎጅም እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

ሚካናይዜሽን አቅርቦት ላይም ከፍተኛ ሚና በመወጣት የስንዴ ጥራቱን ጠብቆ እንዲመረት የሚያደርግ ፕሮጀክት መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳዳር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አራት ወረዳዎች በእዚህ ፕሮጀክት ስለመታቀፋቸው ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ወደ ዞኑ መምጣቱ ስንዴ ከዚህ በፊት ሲለማ ከነበረው በተሻለ መንገድ በማምረት ምርታማነትን ለመጨመር ያግዛል ነው ያሉት፡፡ ፕሮጀክቱ በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ስለመጠናቀቃቸውም ገልጸዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻውን ጨምሮ በግብርና ሚኒስቴር እና በፕሮጀክቱ ብሔራዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብዱልሰመድ አብዶ፣ የዞን ግብር መምሪያ ኀላፊዎች፣ በፕሮጀክቱ የታቀፋ የወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች፣ የቡድን መሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ሰሎሞን ስንታየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአረጋውያን ቀን አከባበር የማጠቃለያ መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው።
Next articleየኤሌክትሮኒክስ ታክስ ክፍያ ሥርዓት የሙከራ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ይፋ ተደረገ።