ቤዛዊት ቤተ-መንግሥት ለቱሪስቶች ክፍት እንዲደረግ ተጠየቀ፡፡

32

ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ከዞን መምሪያዎች እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር ትናንተት በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል፡፡

በመድረኩ በአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት አሥተዳደር እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አበራ ፈንታሁንን ጨምሮ የቢሮው እና የተጠሪ ተቋማት መሪዎች፣ የዞን መምሪያ ኀላፊዎች እንዲሁም የቢሮው የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡

በግምገማ መድረኩ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተከናወኑ የቢሮው እና የተጠሪ ተቋማት የተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል፡፡
በሩብ ዓመቱ እንደ ተቋም የተሠሩ ሥራዎች በአብዛኛው የሚበረታቱ መኾናቸው በተወያዮች ተገልጿል፡፡
በተለይም ክብረ በዓላትን በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ በድምቀት እንዲከበሩ የተደረጉ ጥረቶች አበረታች መኾናቸው ተነስቷል፡፡
በቀጣይም አዳዲስ ሁነቶችን በጋራ ማክበር እንደሚገባ እና የቱሪስት መዳረሻዎችም በስፋት መተዋወቅ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

በክልሉ ያሉ የቅርሶች ጥገና ጊዜ የማይሰጠው እና ከወደሙ ድጋሚ የማይገኙ በመኾናቸው ክትትል እየተደረገ ጥገና እንዲደረግላቸውም በውይይቱ ተነስቷል፡፡ በየዞኖች ያጋጠሙ የአሠራር ተግዳሮቶችም በስፋት ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ዓባይ ወንዝ ዳርቻን ተከትሎ በደቡባዊ አቅጣጫ በኩል ቤዛዊት ኮረብታ ላይ የሚገኘው የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ቤተ-መንግሥት ለቱሪስቶች ክፍት እንዲደረግም ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡
ቤተ-መንግሥቱ በታሪካዊነቱም ኾነ በመልካምድራዊ አቀማመጡ በከተማዋ ከሚገኙ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ በመኾኑ ለጎብኝዎች ክፍት እንዲደረግ የአካባቢው ሕዝብ በተደጋጋሚ እየጠየቀ በመኾኑ ክፍት ሊኾን እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የቢሮው ኀላፊ መልካሙ ፀጋዬ በተሳታፊዎች የተነሱት የአሠራር ተግዳሮቶችን በቀጣይ ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ሥራዎችን በሚገባ በማከናወን የክልሉን የቱሪዝም መስህብ ሃብቶች ለማስተዋወቅ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

የባሕል እና ቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ተዋናዮች የሚሳተፉበት እና በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ ምንጭ በመኾኑ የተቋሙ የሥራ ኀላፊዎች በየደረጃው ካለው የሥራ ኀላፊ ጋር በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸው አቶ መልካሙ ማስገንዘባቸውን ከክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዲጂታላይዜሽን የሪፎርም ሥራዎች በምህንድስናው ዘርፍ ኮርፖሬሽኑን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ናቸው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleበሃሳብ የፀናች እና በምክክር የቀናች ሀገር መገንባት ያስፈልጋል!