
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጋር በወቅታዊ የሰላም እና ደኅንነት ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በሰላም ውይይቱ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የአሥተዳደር ሠራተኞች እና በየደረጃው ያሉ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ተገኝተው ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ መምህራን ሰላም ለሁሉም ነገር ወሳኝ ነው፤ የሰላምን ጠቀሜታ ማንኛውም ሰው የሚዘነጋው አይደለም ብለዋል፡፡ ለሰላም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ መንግሥትም በሆደ ሰፊነት የጀመረውን የሰላም አማራጭ አጠናክሮ ይቀጥል ብለዋል።
የውይይት መድረኩ ማኅበረሰቡ የግንዛቤ ደረጃውን እንዲያሳድግ ስለሚያግዝ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዚዳንት ጋሻው ግስሙ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው የአንድነት እና የኅብረ ብሔራዊነት መገለጫ እንደመኾኑ ለሰላም ያለው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም ነው ያሉት፡፡ መምህራንም ማስተማር ያለባቸው በዚህ ደረጃ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ደማሙ ሃብቴ ሰላም ከገበያ አይገዛም፤ ሰላምን የሚፈጥረው እና የሚጠብቀው ማኅበረሰቡ ነው፤ ሁሉም ለሰላም በሩ ክፍት ሊኾን ይገባል ብለዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው ለሰላም የምሁራን ሚና የላቀ ነው፣ ምሁራኑም ገንቢ ሃሳቦችን በማዋጣት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
እስካሁን ምሁራኑ ለሰላም ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚበረታታ መኾኑን የተናገሩት ዋና አሥተዳዳሪው ለወደፊቱም ይሄ መልካም አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!