
ደሴ ፡ ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተመራቂ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተመራቂ ወላጆች ተገኝተዋል።
በኮምቦልቻ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ምክትል ሳይንቲፊክ ዳይሬክቴተር ሀብታሙ መሐመድ (ዶ.ር) “ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር እራሳችሁን እና ሀገራችሁን እንድትለውጡ” ብለዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ.ር) በ2016 ዓ.ም ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ከ12 በላይ ምርምሮችን ከብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የምርምር ፕሮጀክቶችን በመፈራረም ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።
የዩኒቨርሲቲው መማክርት ጉባኤ ባካሄደው ሥብሠባ በመደበኛ፣ በክረምት፣ በርቀት እና በተከታታይ መርሐ ግብሮች በቅድመ እና ድኅረ ፕሮግራሞች 2 ሺህ 224 ውጤታቸው ተመርምሮ የፀደቀላቸው እጩ ምሩቃንን ለማስመረቅ ስለመዘጋጀታቸውም ነው የገለጹት።
ዶክተር አወል ሰይድ በኮምቦልቻ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ዛሬ ለተመረቁ 199 እጩ ተመራቂዎችም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ለተመራቂዎች መልዕክት ያስተላለፉት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድ አሚን የሱፍ ሀገሪቱ ቴክኖሎጅን በሚገባ ከተጠቀመች ካደጉ ሀገራት ተርታ መሰለፍ እንደምትችል ጠቁመዋል።
ዛሬ በቴክኖሎጅ ዘርፍ የተመረቁ ተማሪዎች ወደ ሥራው ሲገቡ በቅንነት እና በታማኝነት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በዕለቱ በከፍተኛ ውጤት እና በማዕረግ የተመረቁ ተማሪዎች የሜዳሊያ እና የዋንጫ ተሸላሚ ሁነዋል።
ዘጋቢ፦ ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!