ሀገር የሚያፈርስ ሃሳብ እና የፖለቲካ አካሄድ ሊወገድ እንደሚገባ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ገለጹ።

29

ደባርቅ: ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደባርቅ ከተማ ከመምህራን እና የትምህርት ዘርፍ ኀላፊዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ምክክር ተካሄደ።

በምክክር ሂደቱ የዞን እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ዓለም ከምን ጊዜውም በላይ የኀይል ሚዛንን ለማስጠበቅ ሽኩቻ ላይ ናት፤ በመኾኑም ለሀገር ክብር እና ሉዓላዊነት ዘብ መቆም ያስፈልጋል ብለዋል።

የውጭ ጠላቶቻችንን ዕኩይ ዓላማ ለማስፈጸም በሀገር ብሎም በክልሉ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው የሰላም ጸር ላይ እየተወሰደ ያለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።

ማንኛውም ዘርን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ ለሀገር የማይጠቅም በመኾኑ ማኅበረሰቡ ከዚህ የተሳሳተ አዙሪት ራሱን ሊያላቅቅ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በጋራ የሚፈቱ እንጅ በተናጠል የሚፈቱ ጥያቄዎች አለመኾናቸውን መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመድረኩ የተሳተፉ መምህራን ስለ ሰላም አስፈላጊነት እና ሌሎች ሃሳቦችን አንስተዋል።

ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያ ከ 3ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ የላት ሀገር በመኾኗ በማንም በሬ ወለደ ወሬ አትፈርስም ሲሉ ነው የገለጹት።

መምህር ለሰላም ሚናው ትልቅ በመሆኑ ልጆችን ማስተማር ቤተሰብን ማስተማር ነውም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አንድ ካልኾን ያሰብናቸውን አናሳካም፤ የክልሉን የሰላም እጦትም መፍታትም አንችልም” ሠልጣኞች
Next articleእስከ አሁን የተመዘገቡ ተማሪዎች 31 በመቶ ገደማ መኾናቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡