“አንድ ካልኾን ያሰብናቸውን አናሳካም፤ የክልሉን የሰላም እጦትም መፍታትም አንችልም” ሠልጣኞች

50

ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች “የሕልም ጉልበት፤ ለእምርታዊ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ሥልጠና ወስደዋል፡፡

መሪዎቹ በሥልጠና ቆይታቸው ለቀጣይ ሥራዎቻቸው ተነሳሽነትን እና ቁርጠኝነትን የሚጨምሩ ሃሳቦችን እንዳገኙባቸው ነው የተናገሩት፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዳንኤል ወርቁ ሥልጠናው በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች አንድ ኾነው የክልሉን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የጋራ አስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት እንዲኖራቸው ለማስቻል ዓላማ ያደረገ እንደ ነበር ተናግረዋል፡፡ በሥልጠናዎቹ በቀረቡት በርካታ ሰነዶች ዕውቀት መጨበጣቸውንም ገልጸዋል፡፡

ብልጽግና የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ለመቀየር ካሰባቸው ሃሳቦች አኳያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ግንዛቤ ስለማግኘታቸው ነው የተናገሩት፡፡

ሲፈጠሩ የነበሩ ብዥታዎችንም ያጠሩበት ሥልጠና እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡ በአመለካከት አንድ በመኾን የሕዝብን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መፍታት እንደሚገባም ከሥልጠናው ግብዓት ስለማግኘታቸው ነው ያረጋገጡት፡፡

የክልሉን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ሃሳቦችም በሥልጠናው መነሳታቸውን አብራርተዋል፡፡ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ሕዝብን በማወያየት ችግሮችን መፍታት ይገባል ያሉት ኀላፊው ክልሉ እየተጎዳ ያለው መደማመጥ እና መግባባት በመጥፋቱ ነው ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡ አንድ ኾኖ ሰላሙን በማረጋገጥ በሰላም እጦት ምክንያት የታጡትን የልማት ሥራዎች ማስቀጠል ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የክልሉን ሕዝብ በአግባቡ ማገልገል ከመሪዎች እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ የተዳከመውን የልማት እንቅስቃሴ ማነቃቃት እና የልማት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ከመሪዎች እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በተሟላ መንገድ ለመሥራት ተቋም በመገንባት ማኅበረሰቡን ማገልገል ይገባል ነው ያሉት፡፡

ሀገር ለመገንባት አንድነት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡ አንድነት በመሪዎች እና በሕዝብ መስረጽ እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡ የሕዝብን አንድነት የሚያስጠብቀው የመሪዎች አንድነት ነው ብለዋል፡፡

ሥልጠናው ይበልጥ ወደ ውስጣቸው እንዲመለከቱ እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል፡፡ ውስጥን በማጥራት አንድ ኾኖ ለመሥራት የሚያስችል አቅም ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ተከባብሮ እና ተደማምጦ መሥራት አለበት ያሉት ኀላፊው አንዱ በአንዱ ላይ የመቀሳሰር እና የመገፋፋት አካሄድ አያስፈልግም ነው ያሉት፡፡ የፖለቲካ ሪፎርሙ እስከታች ድረስ ስኬታማ ኾኖ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ስመኘው ተሻገር ሥልጠናው የመሪዎችን አቅም የገነባ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ሥልጠናው ሀገራዊ ሁኔታውን የዳሰሰ እና ግንዛቤ ያስጨበጠ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት የሚያስችሉ አቅም እና ቁርጠኝነትን እንደፈጠረላቸውም ነው የገለጹት፡፡

የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ በአገልጋይነት መንፈስ እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት ቁርጠኞች መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሰላም ለሁሉም ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊው ሰላም ከሌለ የልማት ጥያቄዎችን መፍታት አይቻልም፣ ጥያቄዎችን ለመፍታት አስቀድሞ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የሰላም ሥራውን ለአንድ ወገን ብቻ መተው እንደማይገባም አመላክተዋል፡፡

ከሰላም ጎን ለጎን የልማት ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ ሕዝብን ያሳተፈ የሰላም እና የልማት ሥራዎች እንደሚጠብቁም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በግጭት ምክንያት ክልሉ በውስብስብ የጤና ችግር ውስጥ ነው” አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ
Next articleሀገር የሚያፈርስ ሃሳብ እና የፖለቲካ አካሄድ ሊወገድ እንደሚገባ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ገለጹ።