“በግጭት ምክንያት ክልሉ በውስብስብ የጤና ችግር ውስጥ ነው” አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ

21

ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።

በግምገማው የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱን ጨምሮ የቢሮው ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የዞን ጤና መምሪያ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የአማራር ሥርዓት ግንባታ ለጤናው ሥራ ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።

በጤናው ዘርፍ ያለውን የአቅም ክፍተት ለመሙላት ሥልጠና እየተሰጠ መኾናቸውን ነው የገለጹት።

ሥልጠናዎችን በማጠናከር የጤና አመራር ሥርዓታችን እያዘመን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

የሰው ኀይሉን ብቃት ለማሳደግ፣ አገልጋይ፣ ሩህሩህ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዘላቂ የጤና ፋይናንስ ሥርዓትን ለመገንባት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

የፋይናንስ ሥርዓቱ ዘላቂ እና አይበገሬ የሚኾነው የተጀመረውን የጤና መድኅን ሥርዓት ማስቀጠል ሲቻል ነው ብለዋል።

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የጤና መድኅን ሥራው ፈተና እንደገጠመው ተናግረዋል።

በጤናው ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖሩንም ገልጸዋል። የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሩን መፍታት ይገባልም ብለዋል።

በግብዓት አቅርቦት፣ ስርጭት እና አጠቃቀም ላይም ጉድለት መኖሩን ነው የተናገሩት።

ያለውን ጉድለት ማስተካከል እና መፍታት ይጠበቃል ብለዋል።

የጤና መሠረተ ልማትን በማሟላት በጤና ተቋማት ግንባታ በኩልም በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የጤና ተደራሽነት እና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ የሚቻለው የግንባታ ሥርዓቱ ሲፋጠን መኾኑንም ተናግረዋል።

የጤና ሥርዓቱን ከወረቀት ነጻ ማድረግ እና በቴክኖሎጅ የተደገፈ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

ለማኅበረሰቡ ፈጣን እና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት ሥርዓት መዘርጋትም ይገባል ነው ያሉት።

የሕክምና መሳሪያዎችን ማሟላትም በትኩረት የሚሠራበት ነው ብለዋል።

ባለሃብቶች በጤናው ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

መልካም ነገሮችን ማስቀጠል፣ ጉድለቶችን ማረም እና ማስተካከል ይጠበቃል ነው ያሉት።

በውይይቱ የጤና መድኅን አፈጻጸም እንደሚገመገምም አንስተዋል። በግጭት ምክንያት ክልሉ በውስብስብ የጤና ችግር ውስጥ ነው ብለዋል።

የወባ ወረርሽኝ ከባለፉት ጊዜያት በተለየ መልኩ መጨመሩንም አስታውቀዋል።

የወባ ስርጭትን ለመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ ቢኾንም የሚጠበቀው ውጤት አልተገኘም ነው ያሉት።

የኮሌራ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከል ላይ መሥራት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

የጤናው ዘርፍ በችግር ውስጥም ኾኖ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ በከፋ የጤና ችግር ውስጥ እንዳይገባ የጤና መሪዎች እና ባለሙያዎች የሠሩት ሥራ የሚያስመሠግን መኾኑን ነው የገለጹት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የክልሉ ሕዝብ በልማት ተጠቃሚ እንዲኾን የማያወላውል አቋም እና አንድነት ይዘናል” ሠልጣኞች
Next article“አንድ ካልኾን ያሰብናቸውን አናሳካም፤ የክልሉን የሰላም እጦትም መፍታትም አንችልም” ሠልጣኞች