
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች “የሕልም ጉልበት፣ ለእምርታዊ ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳር ሥልጠና ወስደዋል፡፡
ሠልጣኞቹ በሥልጠናው ውስጣዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ፣ ኀላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት የሚያነሳሱ እና ሌሎች በርካታ ጥቅሞችን እንዳገኙበት ገልጸዋል፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ኢንስፔክሽን እና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ኀላፊ በዕውቀቱ ገዛኸኝ በሥልጠናው የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሃሳብ ያሸንፋል፣ ሃሳብ ያሻግራል፣ ሃሳብ ይጥላል ያሉት ኀላፊው በሥልጠናው የፓርቲውን አውራ እና ሀገር ለማሻገር የያዛቸው ሃሳቦች ላይ የጋራ ሃሳብ እንዲይዙ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ሀገር እንዳትራመድ አስረው የያዙ ትርክቶችን በብሔራዊ ትርክቶች እየተካ እንደሚሄድም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በነጠላ ትርክቶች ብቻ ወደ ፊት መጓዝ እንደማትችል ነው የተናገሩት፡፡ ቀድማ የሠለጠነች እና ታላቅ የነበረች ሀገር የጋራ ባልኾኑ ትርክቶች ወደፊት መራመድ እንደተቸገረች አንስተዋል፡፡
ክልሉ በበርካታ ፈተናዎች እያለፈ ያለ ክልል መኾኑን ያነሱት ኀላፊው አሁን በገጠመው ችግር ምክንያት የሕዝብን ጥያቄዎች መመለስ አልተቻለም ነው ያሉት፡፡ በክልሉ ለተፈጠረው ችግር መልካም አሥተዳደር እና የነጠላ ትርክት ምክንያት መኾኑንም አንስተዋል፡፡
መሪዎች የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመንቀል ሕዝቡ የሚተማመንበት እና የኔ ነው የሚለው አሠራር መትከል እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩ ተማሪዎች እንዳይማሩ፣ ልማት በተፈለገው ልክ እንዳይለማ ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡ የክልሉን ችግር ለመፍታት እና ሕዝቡን ከስቃይ ለማላቀቅ በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ መሪዎች ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችን መሥራታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የክልሉን ሰላም ሙሉ ለሙሉ በማረጋገጥ ለሀገር ያለውን አስተዋጽኦ ከፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ክልሉን በሰላም እና በልማት የተሻለ ለማድረግ ቁርጠኞች መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ በልማት ተጠቃሚ እንዲኾን የማያወላውል አቋም እና አንድነት ይዘናል ነው ያሉት፡፡ የመሪዎች አንድነት ከሌለ የሕዝብ አንድነትን ማምጣት እንደማይቻል ነው የተናገሩት፡፡ የፖለቲካ ግንዛቤ አናሳ ሲኾን የውስጥ አንድነት እንደሚናጋም አንስተዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ አብዮት ሳይኾን ለውጥ ነው ያደረገው ያሉት ኀላፊው በለውጥ ሂደት ውስጥ ደግሞ የአስተሳሰብ መዛነፎች እና መቀላቀሎች ይኖራሉ ብለዋል፡፡ የአስተሳሰብ መዛነፎች የሚጠሩት በሂደት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ፓርቲው የአመራር ማጥራት ሥራ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የአስተሳሰብ መቀላቀል እና ያልጠራ ሃሳብ ያለው መሪ ደግሞ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደማይችልም አመላክተዋል፡፡
አሁን ያሉ መሪዎች አንድነታቸውን ጠብቀው የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እየተንቀሳቀሱ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በለውጥ ሂደት ውስጥ አስተሳሰብን እንደ ብርጭቆ በአንድ ቀን ለቅልቀው የሚደፉት አይደለም፣ የሚጠራው በሂደት እና ቀስ በቀስ ነው ብለዋል፡፡ በተደጋጋሚ የሚሰጡ ሥልጠናዎችም አመለካከትን ለማጥራት ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውን ነው የተናሩት፡፡ ፓርቲው በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ በሥልጠናው አሁናዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን እና በቀጣይ ሊፈጸሙ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ መገኘቱን ነው የተናገሩት፡፡ ፓርቲው አሳካቸዋለሁ ብሎ የያዛቸውን ሕልሞች ለማሳካት እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማምጣት አሁን ያሉብንን ተግዳሮቶች መለየት አስችሏል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይ ከመሪዎች የሚጠበቀውን እና አሁን ያሉ ለውጦችን በምን መልኩ እያስተናገዷቸው እንደኾነ የሚያመላክት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በሥልጣናው በርካታ ተሞክሮዎችን መለዋወጣቸውንም ገልጸዋል፡፡ እንደ ክልል በርካታ የተፈጥሮ ሃብት እና የሚሠራ የሰው ኀይል አለን ያሉት አፈጉባኤዋ ያለውን ኀይል አስተባብሮ የተሻለ ክልል አድርጎ ማውጣት ይገባል ብለዋል፡፡ የክልሉን ኢኮኖሚ ሊያሳድግ፣ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን ሊያስተሳስር የሚችል፣ ለቀጣይ ትውልድም የሚተርፍ ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሥልጠናው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በተመለከተ ግንዛቤ መፈጠሩን ነው የተናገሩት፡፡ ሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚመለከቷት እና የዲፕሎማሲ ሥራዎች እያስገኙት ያሉትን ውጤቶች በሥልጠናው መታየቱንም ገልጸዋል፡፡
የምንገነባቸው ተቋማት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ሊያመጡ የሚችሉ፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታን የሚያሳምሩ፣ ገዥ ትርክትን የሚተክሉ መኾን አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡ የመሪዎች ሥነ ምግባር የተስተካከለ፣ የአገልግሎት አሰጣጡ ሕዝብን ያረካ እና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲኾን ለማድረግ ዝግጁ የኾንበት ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡ ጥሩ ተሞክሮዎችን የበለጠ በማስፋት፣ ጉድለቶችን ደግሞ በማረም፣ በቀጣይ የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት ስንቅ እና ትጥቅ የያዙበት ሥልጠና እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
በሥልጠናው የተገኙ ሃሳቦችን በቁርጠኝነት እንደሚፈጽሙም ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው አቅም እና ቁርጠኝነትን የፈጠረ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ በተለይም ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት ሰላምን ማጽናት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ ከሰላም ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ የተናገሩት አፈጉባኤዋ የልማት ሥራዎች ባደጉ ቁጥር ሰላምንም ማጽናት እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡ ክልሉ ካለበት የሰላም ችግር ለመውጣት በርካታ የሰላም አማራጮች ተቀምጠው እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ክልሉን በአጭር ጊዜ ወደ ተሟላ ሰላም መመለስ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ ክልሉ በልማት የተሻለ እስካልኾነ ድረስ የሚፈለገው ሰላም እንደማይረጋገጥም ተናግረዋል፡፡ ክልሉ ተወዳዳሪ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን የመሪዎችን ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!