
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በድኅረ ምርት ወቅት የምርት ብክነት እንዳያጋጥም በወቅቱ መሠብሠብ እንደሚገባ በቢሮው የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2016/17 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሠራ ይገኛል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በምርት ዘመኑ ምርታማነትን ለማሳደግ ከ2015/16 የምርት ዘመን በተሻለ የማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ማሰራጨት ተችሏል፤ አርሶ አደሩም ማሳውን በድግግሞሽ ከማረስ ጀምሮ ሰብሉን በወቅቱ እንዲንከባከብ እና በተለያዩ ተባዮች እንዳይጠቃ የአሰሳ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
አሁን ላይም ለመሠብሠብ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በኮምባይነር ጭምር ታግዞ የመሠብሠብ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። እስከ አሁንም ከ450 ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል ተሠብሥቧል።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ ሰሊጥ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ መሰል ሰብሎች ይገኙበታል። ሰሊጥ ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
በቀጣይም ሰፋፊ እርሻ ባለባቸው እና ምቹ በኾኑ ቦታዎች በኮምባይነር ታግዞ እንዲሠበሠብ ይደረጋል ብለዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ በቅድመ ምርት በተሰጠው ትኩረት ልክ በድኅረ ምርት ወቅት ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት ለመቀነስም ትኩረት መሰጠቱን ነው የገለጹት።
ምርቱ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ እንዲቀመጥ እና ለተባይ እንዳይጋለጥ የሚያግዙ የፕላስቲክ ከረጢቶች እና በቀላሉ መንቀሳቀስ የሚችሉ የብረት ጎተራዎች ለአርሶ አደሮች እየተሠራጨ ይገኛል።
አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እንዲሠበሥቡ፣ ከሠበሠቡ በኋላም ለዝናብ እና ለተለያዩ ተባዮች እንዳይጋለጡ በተገቢው መንገድ ማስቀመጥ እና ቶሎ ወቅቶ ወደ ጎተራ እንዲያስገቡ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!