
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች “የሕልም ጉልበት፣ ለእምርታዊ ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳር ሥልጠና ወስደዋል፡፡
መሪዎቹ በሥልጠናው የሃሳብ እና የተግባር አንድነት በሚያመጡ፣ የክልሉን፣ የሀገሪቱን፣ የቀጣናውን እና የዓለምን ሁኔታ በሚያመላከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና ወስደዋል፡፡ ሀገራዊ አንድነትን፣ ኅብረ ብሔራዊነትን፣ ዕድገትን እና ልማትን የሚያመጡ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም ሠልጣኞቹ ተናግረዋል፡፡ መሪዎች ሀሰተኛ ትርክትን ማስተካከል፣ ሀገራዊ እና ዕውነተኛ ትርክትን ደግሞ ማጽናት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ንጉሤ ትርክት ሀገር ያፈርሳልም፤ ትርክት ሀገርም ይገነባልም ብለዋል፡፡ ትርክቶችን ለአብሮነት እና ለአንድነት፤ ለሀገር እና ለሕዝብ ማሻገሪያነት ከተጠቀምንባቸው ትውልድ እና ሀገር የሚገነቡ ይኾናሉ ነው ያሉት፡፡ የጋራ ወይም የወል ዕውነት የምንላቸውን ትርክቶች ከሠራን በጋራ የምንሻገርባቸው ይኾናሉም ብለዋል፡፡
የኔ ብቻ ወይም ሁልጊዜም የእኔ ነው ትክክል፣ የሌሎች ልክ አይደለም በሚል እሳቤ የሚወሰዱ ትርክቶች መለያየትን፣ መራራቅን፣ አብሮ ያለመኾንን እያሰፉ ሀገር እንደሚያፈርሱ ነው የተናገሩት፡፡ የምንገነባቸው ትርክቶች ለጋራ፣ ለአብሮነት እና ለአንድነት የሚጠቅሙ መኾን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ የጋራ እና አንድነትን የሚገነቡ ትርክቶችን ለመገንባት መሪዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም አመላክተዋል፡፡
የተናጠል ዕውነታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሀገራዊ ዕውነታውን መርሳት ተወዳደሪነት እና ተፎካካሪነት እየታጣ እንደሚሄድም ገልጸዋል፡፡ የጋራ ዕውነት መገንባት ለሀገር ትልቅ ጥቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ለጋራ ዕውነት፣ ለጋራ ኀላፊነት ራስን ማሳመን እና አካባቢን ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ገዥ ትርክቶችን መገንባት ከተቻለ ሀገር መገንባት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡ በጋራ መሥራት ለውጥ እንደሚያመጣም ገልጸዋል፡፡
የተማረ ሰው አስታዋይ እና አርቆ አሳቢ፣ ለዛሬ ብቻ ሳይኾን ለነገም የሚያስብ መኾን አለበት ያሉት ኀላፊዋ ምሁራን ሀገራዊ አንድነትን የሚገነቡ ታሪኮችን በማውጣት ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የታሪክ ተወቃሽነት እንዳይመጣ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡ ሀገር የሚገነባው በጋራ መቆም መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ለሀገር በጎ ሥራ የሠሩ ሰዎችን ማሰብ እና የእነርሱን አርዓያነት ለሀገር ግንባታ መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ የሚያፈርሰውን ሳይኾን አንድ የሚያደርገውን ሃሳብ ማሰብ ይገባልም ብለዋል፡፡
ነገ የዓለም ሀገራት የሚፈሯት ኢትዮጵያን ለመፍጠር መልካም የሠሩ አባቶችን አርዓያነት ይዞ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡ አፍራሽ ሃሳቦችን መተው እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ለትውልድ ሲባል ይቅርታ ማድረግ እና መግባባት እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ትናንትን በአግባቡ መረዳት፣ ዛሬንም በአግባቡ መኖር አለብን፣ እነዚህን ስናደርግ ነገን እናሳምራለን ነው ያሉት፡፡ ትናንት ማኅበራዊ ትስስርን ከፍ የሚያደርጉ፣ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው የተረዳዱበት እና ሌሎች መልካም ነገሮች መሠራታቸውን የሚያነሱት ምክትል አሥተዳዳሪው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የተከበረበት የጀግንነት ታሪክም አለን ይላሉ፡፡ መልካም ነገሮችን በደንብ አጉልቶ ማውጣት እና ለዛሬ እርሾ ኾነው እንዲቀጥሉ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡
ትናንት ጥሩ ያልኾኑ ታሪኮች ተሠርተው ሊኾን እንደሚችል የሚያነሱት ምክትል አሥተዳዳሪው ዛሬ ላይ እንዳይደገሙ ማድረግ ይገባል፤ የትናንት መልካም ነገሮችም ኾነ ጥሩ ያልኾኑ ታሪኮች የጋራ ታሪኮቻችን እንደኾኑ ማሰብ እና ሁለቱን አስታርቆ መሄድ ይገባል ብለዋል፡፡ እንደ ሀገር የተያዘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጋራ ትርክት እንዲፈጠር እንደሚያደርግም አንስተዋል፡፡
በሀገራዊ ምክክሩ የሚያግባቡ ጉዳዮችን አጉልቶ ማውጣት የማያግባቡ ነገሮችን ደግሞ መልክ እንዲይዙ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የማያግባቡ ታሪኮች በታሪክ የራሳቸው ቦታ እንዲሰጣቸው ቢደረግም የአሁኑን ዘመን እንዲያበላሹ ማድረግ ግን አይገባም ብለዋል፡፡ ነጠላ ትርክት እየከረረ ሲሄድ ኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊነት የሚለው ትርክት እየላላ ይሄዳል ነው ያሉት፡፡ አንድነት ሲላላ እንደ ሀገር በጋራ የመቆም ችግር ሲገጥም በጋራ የመጋፈጥ እና ድህነትን በጋራ ታግሎ የማሸነፍ ዕድል እየተመናመነ እንደሚሄድ ነው ያመላከቱት፡፡
ኅብረ ብሔራዊ የኾነ፣ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን መሠረት ያደረገ ብሔራዊ ትርክትን መገንባት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡ ኅብረ ብሔራዊነትን፣ ወንድማማችነትን እና አንድነትን ከፍ የሚያደርጉ የፖለቲካ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡ የሚመጣው ትውልድም መግባባት የሚችልባት ሀገር መፍጠር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የታሪክ ምሁራን ሀገራዊ እና ገዥ ትርክትን ለመፍጠር ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡ የሁሉንም ወገኖች ሃሳብ መጠቀም እና የጋራ የኾኑ ሃሳቦችን ማጉላት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ የተናገሩት ምክትል አሥተዳዳሪው ነገር ግን በስሁት ትርክት እንደጨፍላቂ፣ እንደ ጨቋኝ ሲታይ ቆይቷል፣ ይሄ ፍጹም ስህተት እና የማንቀበለው ነው ብለዋል፡፡ የጋራ ትርክት መገንባት ስሁት ትርክቶችን ትክክለኛ መልክ እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ በሀገራዊ ምክክሩ የአማራ ክልል ሕዝብ ለኢትዮጵያ የዋለው ውለታ በልኩ እና በመልኩ በደንብ መገለጥ አለበትም ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያ እዚህ እንድትደርስ በላቡ እና በደሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ እንጅ በታሪክ ውስጥ የሚወቀስ አይደለም ነው ያሉት፡፡ ይሄን ዕውነታ ደግሞ ማስጨበጥ እና መስገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ገብረማርያም መንግሥቴ በኢትዮጵያ ሀገር እስከማሳጣት ድረስ ሊያደርሱ የነበሩ የተዛቡ ትርክቶች መፈጠራቸውን ገልጸዋል፡፡ የተዛቡ ትርክቶች ያመጡት ችግር እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ አሁንም ወደ ተሟላ ሰላም ለመምጣት ዋጋ እያስከፈሉ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡ የሚያሠባሥቡ እና አንድ የሚያደርጉ ትርክቶችን ማጎልበት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የጋራ ትርክት ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብም በተዛቡ እና በሀሰተኛ ትርክቶች ብዙ መከራዎችን እና ግፎችን እንደተቀበለ አስታውሰዋል፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ማንነትን እስከመንጠቅ የሚያደርስ ሀሰተኛ እና የተዛባ ትርክት ተዘርቶ እንደኖረም አስታውሰዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ተፈጥሯዊ ወሰን፣ ትክክለኛ ማንነት እና ዕውነትን በመካድ ሀሰተኛ ትርክት ተሠርቶበት ነበር ነው ያሉት፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ዕውነት እና ትክክለኛ ታሪክ በዘርፈ ብዙ ማስረጃዎች እንደተቀመጠም ገልጸዋል፡፡ ዕውነተኛ ማንነትን ሊነጥቅ የሚችል ምንም ጉዳይ ሊኖር አይገባም ብለዋል፡፡
ከእንዲህ ዓይነት ሀሰተኛ ችግር ለመውጣት ዕውነት ላይ የተመሠረተ ትርክት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ዘላቂ መፍትሔ የሚመጣው በዕውነት ላይ የተመሠረተ ትርክት ሲኖር እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ በዕውነት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ እንደሚኾን የተናገሩት ኀላፊው የተዛቡ ትርክቶችን ለማረም ዕውነትን መቀበል ያስፈልጋል፣ በሀሰት የተደበቀ ነገር ሀገር ሊያሻግር አይችልም ነው ያሉት፡፡ ሀሰተኛ ትርክት በማኅበረሰብ ዘንድ መራራቅን በመፍጠር ለዕድገት እንቅፋት እንደሚኾንም ተናግረዋል፡፡
አሁን የጋራ እና ሀገራዊ የኾኑ ትርክቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ተስፋ ሰጭ ጅማሮዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ አንድነትን ለመገንባት የሁሉም ድርሻ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ማስቀደም ሲቻል የተሻለ ሀገር መገንባት እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡ ለጋራ ሀገር በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎችን ፈጥኖ ምላሽ መስጠት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ለሀገራዊ ትርክቱ መሠረት እንዲኾን እና መገፋፋቶች እንዳይኖሩ ፈጥኖ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!