
ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና ቁጥጥር የሥራ ክፍል አሥተባባሪ ደምሌ ካሳ በዞኑ ካሉት 13 ወረዳዎች ውስጥ በሰባቱ የወባ በሽታ በስፋት መከሰቱን። እንደ አስተባባሪው ገለጻ የሰባቱ ወረዳዎች የወባ ሽፋን የዞኑን 93 በመቶ ይሸፍናሉ ብለዋል።
ወቅቱ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ በመኾኑ ከፍተኛ የወባ ክስተት የታየበት ነው ብለዋል። በያዝነው ዓመት እስከ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም ድረስ 23 ሺህ 327 የወባ በሽታ ታማሚዎች ሪፖርት ተደርጓል። ከባለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ102 በመቶ ብልጫ አለው ነው ያሉት።
በወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት አለመቻሉ፣ የወባ መድኃኒት መቆራረጥ፣ የበጀት እጥረት እና የኅብረተሰቡ ተሳትፎ በቂ አለመኾን ያጋጠሙ ችግሮች መኾናቸውን አሥተባባሪው ጠቁመዋል። የወባ በሽታ እስከ ታኅሳስ መጨረሻ ድረስ ሊቀጥል የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ እንደኾነም አንስተዋል። ዞኑ የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች እገዛዎችንም እንደሚፈልግ ነው አሥተባባሪው አሳውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!