26

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የወባ በሽታ ሥርጭት ካለፉት ዓመታት በተለየ ኹኔታ የኀብረተሰቡ ጤና ሥጋት እየኾነ ይገኛል። በአማራ ክልል ከፍተኛ የሰው ፍሰት በሚታይባቸው አካባቢዎች፣ በኢንቨስትመንት እና ቆላማ ቦታዎች የበሽታው ሥርጭት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

ሥርጭቱ እየጨመረ ከመጣባቸው አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ ደቡብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። በደራ ወረዳ አምበሳሜ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት ቄስ ብርሃን ደምሌ አካባቢው በተለይም በሰኔ እና መስከረም ወራት ላይ የወባ ሥርጭቱ በፊት ከነበረው መለየቱን ገልጸዋል። የሦሥት ወር ሕጻን ልጃቸው በወባ በመጠቃቱ በአንበሳሜ ጤና ጣቢያ ለሕክምና እንደመጡ ገልጸዋል።

ሌላዋ ያነጋገርናቸው ምክር መስፍን የአራት ዓመት ሕጻን ልጃቸው በወባ መጠቃቱን ገልጸዋል። ቤተሰባቸውም በተደጋጋሚ በወባ በሽታ መጠቃታቸውን ገልጸዋል። በደራ ወረዳ የአንበሳሜ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ጌታሰው አባተ አካባቢው ከፍተኛ ሕሙማን መመዝገቡን ገልጸዋል። በቀን በጤና ጣቢያው ከሚታየው እስከ 300 የሚደርስ ሕሙማን 150 የሚኾኑት የወባ ተጠቂዎች ናቸው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ሕጻናት ይበልጥ ተጠቂዎች ናቸው።

የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ መረጃ እንደሚያሳየው ከሐምሌ 1/2016 ዓ.ም እስከ መስከረም 20/2017 ዓ.ም የወባ ምርመራ ካደረጉት 199 ሺህ 412 ሰዎች ውስጥ 86 ሺህ 884 በወባ ተጠቅተዋል። ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 54 በመቶ ጭማሪ አለው።

ከጠቅላላ ሕሙማን ውስጥ 13 በመቶ ከ5 ዓመት በታች ሕጻናት፣ 28 በመቶ ከ5 እስከ 14 ዓመት የሚገኙ፣ 59 በመቶ የሚኾኑት ደግሞ ከ15 ዓመት በላይ የሚኾኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቂዎች ናቸው። በአብዛኛው አምራች የኾነው የሰው ኀይል በወባ እየተጠቃ እንደሚገኝ መረጃው ያመለክታል።

በዞኑ ከሚገኙ 14 ወረዳዎች ውስጥ ደራ፣ ፎገራ፣ ሊቦ ከምከም፣ አንዳቤት እና ፋርጣ ወረዳዎች የሚገኙ 240 ቀበሌዎች ከፍተኛውን የወባ ሥርጭት ይሸፍናሉ። በደራ፣ ፎገራ እና እብናት በሚገኙ 21 ቀበሌዎች የወባ ኬሚካል ርጭት ተካሂዷል። 50 ሺህ 770 ቤቶችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። በዚህም 124 ሺህ 242 ሰዎችን መጠበቅ ተችሏል።

16 ሺህ 459 ሜትር ስኩዬር የሚኾን ቦታ የማፋሰስ፣ የማዳፈን እና የማጨድ፣ 370 ሜትር ስኩዬር ለማፋሰስ በማይቻል ውኃማ አካላት ላይ ደግሞ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የኬሚካል ርጭት ተደርጓል። ለ698 ሺህ 910 ሰዎች የወባ በሽታን መከላከል በሚቻልበት ኹኔታ በተለያዩ አማራጮች የጤና ትምህርት ተሰጥቷል።

ይሁን እንጅ በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሚጠበቀው ልክ ቤት ለቤት ተዘዋውሮ መሥራት አለመቻሉም ተገልጿል። ማኅበረሰቡም ለአካባቢ ቁጥጥር ሥራ የሰጠው ትኩረት ደካማ መኾኑ እና የአጎበር አጠቃቀም ባሕል አለማደጉ በተፈለገው መጠን መከላከል እንዳልተቻለ ከዞኑ ጤና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አሳሰበ፡፡
Next articleየወባ በሽታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።