
ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ ይዘንጋው መኮንን ገልጸዋል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የወባ በሽታ ቁጥር 47 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ተናግረዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ በጭስ ዓባይ ክላስተር፣ ወረብ ክላስተር፣ ጣና ክፍለ ከተማ እና ወራሚት የወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ የታየባቸው አካባቢዎች እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡ በከተማው የወባ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው በአየር ንብረት ለውጥ መኾኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ የኅብረተሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ አናሳ መኾንም ለስርጭቱ መስፋፋት ሌላው ምክንያት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
የአጎበር ስርጭት አለመኖር እና የወባ ትንኝ እጮችን መግደያ ኬሚካል ያለመኖርም ስርጭቱ በከፋ ሁኔታ እንዲባባስ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡ እንደ ከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ የወባ ስርጭቱን ለመቆጣጠር የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በየትምህርት ቤቶች እና ቤት ለቤት በመሄድ የግል እና የአካባቢ ንጽህናን ከመጠበቅ ጀምሮ ውኃ ያቆሩ አካባቢዎችን የማፋሰስ እና የማዳፈን፣ የተቃጠለ ዘይትን በመጠቀም የወባ መራቢያ ቦታዎችን የመርጨት፣ አጎበርን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እና የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እንዲሠሩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ማንኛውም ሰው የሕመም ስሜት ሲሰማው ፈጥኖ በአካባቢው ወደሚገኝ የህክምና ተቋም ሄዶ በመመርመር የታዘዘለትን መድኃኒት ሳያቋርጥ መውሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!