ኅብረተሰቡ ለወባ በሽታ ስርጭት ትኩረት ባለመስጠቱ የከፋ ጉዳት እየደረሰ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

43

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ወባ ትልቁ የጤና ችግር እየኾነ መምጣቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ የኀብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ አሕመድ ዓሊ አስረድተዋል፡፡ አቶ አሕመድ ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 121 ሺህ 110 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው 47 ሺህ 79 የሚኾኑ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ የወባ በሽታ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር አሁንም ትኩረት የሚሻ የማኅበረሰቡ የጤና ጠንቅ ኾኖ ቀጥሏል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የወባ ሕሙማንን ሪፖርት እንደሚያደርጉም ነው ያስረዱት፡፡ ዞኑ የልማት ቀጣና በመኾኑ በርካታ ሰዎች ወደ አካባቢው ይገባሉ እነዚህም ከነዋሪው በተጨማሪ ለወባ ተጋላጭ መኾናቸውን ነው የጠቆሙት፡፡

የአካባቢው ነዋሪ አጎበርን ጨምሮ እርጭት በማድረግ እና በሌሎችም የመከላከያ ዘዴዎች ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ቢኾንም ወደ ቀጣናው የሚመጣው የሰው ፍሰት ግን ወባን በተመለከተ ጥንቃቄ ስለማያደርግ ተጋላጭነቱ ሰፊ ኾኖ መታየቱን ነው ያብራሩት፡፡ የወባ በሽታን ለመከላከል በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር ፈታኝ እየኾነባቸው መምጣቱን ነው ያረጋገጡት፡፡

ሰዎች እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው መድኃኒት ለማግኘት እና ለመታከም ባለመቻላቸው የወባ በሽታን መቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው ነው ባለሙያው የሚናገሩት፡፡ የወባ በሸታ በአየር ንብረቱ መቀያየር፣ በሕዝብ ቁጥር መጨመር እና በዝናቡ ወጣ ገባ መኾን ለወባ መጨመር ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ነው ያመለከቱት፡፡

በዞኑ የክስተት አሥተዳደር ሥርዓት ተቋቁሞ ወባን ለመከላከል ሰፊ ርብርብ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ማለትም ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ፣ ለወባ ትንኝ አመች ሊኾኑ የሚችሉ እጽዋትን የማጨድ እና የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

የአጎበር አጠቃቀምን በተመለከተም በየቀበሌው ያሉ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በመጠቀም ቤት ለቤት የአጎበር አጠቃቀም ትክክለኛነትን እያረጋገጡ እና ትምህርት እየሰጡ ነው። ለነፍሰ ጡር እና ለሕጻናት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው እየተደረገ ነውም ብለዋል። ሕክምናውን በተመለከተም የጤና ኬላዎች በትኩረት ይዘው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነት የተቋቋመ ስምንት የተንቀሳቃሽ ሕክምና ቡድን የመከላከል ሥራ እየሠራ ነው።

በሽታው በብዛት ይከሰትባቸዋል በተባሉ ቦታዎች እና የቀን ሠራተኞች በሚገኙባቸው የልማት ቀጣናዎች እየተንቀሳቀሰ እያከሙ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ በዞኑ የመማር ማስተማር ሥራ በመጀመሩ ከትምህርት ቤቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

“ወባን ለማጥፋት ከእኔ ይጀምራል” በሚል የወባ ሳምንትን እየተካሄደ ነው ተብሏል፡፡ በተለይ በዞኑ ያሉ ባለሃብቶች የራሳቸው የጤና ባለሙያዎች እንዲኖሯቸው የሚጠበቅ ቢኾንም አሁን ላይ ያላቸው ጥቂት ናቸው ብለዋል፡፡ ባለሙያው ባለሃብቶች ለሠራተኞቻቸው ጥንቃቄ ቢያደርጉ ሲሉም መክረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጎንደር ዩኒቨርሲቲው እምቦጭን ለባዮ ጋዝ መጠቀም የሚያስችል አዲስ የምርምር ውጤት ወደ ተግባር ለማሸጋገር እየሠራ ነው፡፡
Next articleሴቶች በዲጂታል ዘርፉ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ መደገፍ እንደሚገባ በለጠ ሞላ (ዶ.ር) አሳሰቡ።