ድኅረ ምርት ብክነት እስከ 30 በመቶ ምርትን እንደሚቀንስ የዓለም እርሻ እና ምግብ ድርጅት አስታውቋል፡፡

63

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰብል ከእሸትነት ደረጃው ጀምሮ ተወቅቶ ወደ ጎተራ እስኪገባ ድረስ የሚባክንባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ሰብል በቁመናው፣ በአጨዳ፣ በክምር፣ በውቂያ፣ በማጓጓዝ እና በማከማቸት ጊዜ እንደሚባክን ይገለጻል። በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ የአጣ ቀበሌ አርሶ አደር አገኘሁ አገዘ ለድኅረ ምርት ብክነት ትኩረት ሰጥተው በጥንቃቄ እንደሚሠበስሥቡ ነው የገለጹት፡፡ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ ማጨድ፣ በክምር ወቅት ከዝናብ፣ ከጎርፍ እና ከምስጥ ተጠንቅቆ መከመር የአርሶ አደሩ ሥራ መኾን እንዳለበትም ተናግረዋል። ለአርሶ አደሩም ማስተማር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ የተለያዩ ባሕላዊ የመከላከል ስልቶችን እንደሚጠቀምም ገልጸዋል። አሁን አሁን ገበሬው ከግብርና ባለሙያዎች በሚሰጡት ትምህርትም ኾነ ከችግሩ እየተማረ ሰብሉ እንዳይባክንበት ጥንቃቄ እያደረገ ነው ይላሉ። ሰብሉ ተወቅቶ ቤት ከገባ በኋላ አላግባብ እንዳይባክንም ኾነ አይጥ እንዳይበላው የጭቃ ጎተራ በጥንቃቄ እንደሚዘጋጅ ነው የተናገሩት።

በወረዳው የአርጋ ድድም ቀበሌ አርሶ አደር ተስፋው ክብረት በበኩላቸው የሰብል ምርት እንዳይባክን በቁመናውም ኾነ ከታጨደ በኋላ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት። የግብርና ባለሙያዎች የድኅረ ምርት ብክነትን ስለመከላከል እንደሚያስተምሩ ነው የሚገለጸው። በባሕላዊ ዘዴ እና ከግብርና በሚገኘው ትምህርት እጠቀማለሁ። አርሶ አደሩም ሳይዘናጋ በጥቅምት ጀምሮ ጎተራ ያዘጋጃል። ሰብል ጎተራ ከገባም በኋላ አይጥ እንዳያባክነው በየጊዜው ቁጥጥር ይደረጋል ነው ያሉት አርሶ አደር ተስፋው።

ሰብል ከታጨደ በኋላ ሲከመር ዝናብ እንዳያበሰብሰው፣ ጎርፍ እንዳይገባበት እና ምስጥ እንዳይበላው በጥንቃቄ ይከመራል ብለዋል። ከውቂያም በኋላ ምርት በኬሻ ተከማችቶ እንደሚቆይ እና ለዚህም የሚያገለግል ከረጢት በግብርና በኩል እንደሚቀርብ ነው የገለጹት። የስርቆትም ኾነ የእሳት አደጋ እንዳያጋጥምም በጥንቃቄ እና በተገቢው ቦታ ይቀመጣል ነው ያሉት።

ድኅረ ምርት ብክነት ማለት ከሰብል ሥብሠባ እስከ ጎተራ ድረስ ያለው ብክነት እንደኾነ ከደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በወቅቱ ባለመሠብሠቡ ደርቆ በመፍሰስ፣ በዝናብ፣ በምስጥ፣ በአይጥ፣ በነቀዝ፣ በክምር፣ በውቂያ፣ በማጓጓዝ ጊዜ እና በቤት ውስጥ በጥንቃቄ ጉድለት የሚደርሱ ብክነቶች ተጠቃሾች ናቸው።

በዓለም የእርሻ እና ምግብ ድርጅት (ፋኦ) ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ በአማካይ 30 በመቶ የድኅረ ምርት ብክነት ይደርሳል። እንደ ደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ገለጻ የድኅረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ እየሠራ ነው። በድኅረ ምርት ብክነት ላይ ግንዛቤው አነስተኛ በመኾኑ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ነው የሚሉት ባለሙያዎች።

ነገር ግን አርሶ አደሩ በሂደት ግንዛቤ እየተፈጠረለት ስለኾነ በማሳም ኾነ ቤት ከገባ በኋላ የምርት ብክነትን እየቀነሰ መኾኑ ተገልጿል። ሰብሉ ሳይረግፍ በመሠብሠብ፣ ክምሩን ዝናብ እንዳይመታው እና ምስጥ እንዳይበላው በመከላከል፣ በቤት ውስጥም የተሻሻሉ ጎተራዎች በመጠቀም እና የነቀዝ መከላከያ ኬሚካሎችን በመጠቀም ብክነትን እየተከላከለ ነው።

እስከ ቀጣዩ ወር ድረስ 30 ሺህ አየር የማያስገባ ባለ1 ኩንታል ከረጢት ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሠራ ነው። ከረጢቱን ማግኘት የማይችሉት እና በሞቃታማ አካባቢዎች ደግሞ ከግብርና ባለሙያዎችን እያማከሩ የነቀዝ መከላከያ ኬሚካልን መጠቀም እንደሚገባቸው ነው ባለሙያው የመከሩት። በእርሻ፣ በዘር እና በአረም ወቅት ምርትን ለመጨመር ትኩረት ተሰጥቶ በርብርብ እንደሚሠራ ሁሉ የድኅረ ምርት ብክነትን ለመቀነስም ርብርብ መደረግ እንዳለበት ነው ሃሳባቸውን ለአሚኮ ያካፈሉ ባለሙያ የገለጹት።

በግብርና ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ሁለተኛው ሩብ ዓመት የትኩረት መስኮች ውስጥም አንዱ መንግሥት የምርት ብክነትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑ ታውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለወጭ ንግድ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ 25 ምርቶችን ወደ ምርት ግብይቱ ማስገባቱን ገለጸ።
Next articleጎንደር ዩኒቨርሲቲው እምቦጭን ለባዮ ጋዝ መጠቀም የሚያስችል አዲስ የምርምር ውጤት ወደ ተግባር ለማሸጋገር እየሠራ ነው፡፡