
ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን በ2016/17 የምርት ዘመን ከ432 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማረስ 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ እየተሠራ ነው። አሚኮ ያነጋገራቸው የወረኢሉ ወረዳ አርሶ አደሮች ስንዴን በኩታገጠም በመዝራታቸው፣ ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው እንዲኹም የተባይ አሰሳ እና ክትትል በማድረጋቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ነው የተናገሩት።
የሰብሉ ቁመና ከአምናው የተሻለ ምርት እንደሚሰጥ አመላካች መኾኑንም ገልጸዋል። ምርታማነታቸውን በሄክታር ከ35 ኩንታል ወደ 45 ኩንታል ለማሳደግ እየሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል። በወረኢሉ ወረዳ 28 ሺህ ሄክታር መሬትን በልዩ ልዩ ሰብሎች በመሸፈን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ እየተሠራ መኾኑን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታቸር ተስፋዬ ተናግረዋል።
በወረዳው በ138 ክላስተር 19 ሺህ ሄክታር መሬትን በስንዴ ዘር በመሸፈን 900 ሺህ ኩንታል ለማምረት መታቀዱን ነው አቶ ጌታቸር የገለጹት። ምርት እና ምርታማነትን በሄክታር በ10 ኩንታል ለመጨመር እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው በምርት ዘመኑ 43 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ እና 27 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉን አንስተዋል።
በዘንድሮው ዓመት ለማግኘት የታቀደው ምርት ከአምናው ተመሳሳይ የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር የ500ሺህ ኩንታል ብልጫ እንዳለውም ነው አቶ ጌታቸር የተናገሩት። በደቡብ ወሎ ዞን በ2016/17 የምርት ዘመን ከ430 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በልዩ ልዩ የሰብል ዝርያዎች በመሸፈን 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መኾኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ አሳልፍ አሕመድ ለአሚኮ ተናግረዋል።
በመኸር ወቅት በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች 202 ሺህ ሄክታር መሬትን በስንዴ ዘር በመሸፈን 8 ሚሊዮን 400ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ተወካይ ኀላፊው ገልጸዋል። በምርት ዘመኑ የስንዴን ምርታማነት ለመጨመር የሚታረሰውን መሬት ሽፋን በ46 በመቶ በማሳደግ ምርትን በ60 በመቶ ለመጨመር እየተሠራ መኾኑን ነው አቶ አሳልፍ የተናገሩት።
በትንሽ መሬት ላይ ሰፊ ምርት ማግኘት ስለሚቻል አርሶ አደሮች ለስንዴ ምርት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በዞኑ ከ490 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና 209 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል ያሉት ተወካይ ኀላፊው የተባይ አሰሳን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ተግባራት በትኩረት እየተሠሩ በመኾኑ ከታቀደው በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ነው አቶ አሳልፍ የገለጹት
በዘንድሮው ዓመት በዞን ደረጃ ለማግኘት የታቀደው ምርት ከአምናው ተመሳሳይ የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር የ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለውም አቶ አሳልፍ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሊ ይመር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!