
ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በቀድሞ ስሟ ላኮመልዛ ትባል የነበረችው ያሁኗ ደሴ ከተማ ከ120 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረች ከተማ ናት፡፡ በአማራ ክልል ከሚገኙት ሦሥት ሜትሮ ፖሊታን ከተሞች ውስጥ አንዷ የኾነችው ደሴ በ10 ክፍለ ከተሞች እና በስድስት የገጠር ቀበሌዎች የተከፋፈለች ውብ ከተማም ናት፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማዋ ደሴ በጦሳ እና አዘዋ ተራሮች የተከበበች፣ ለሰው ልጅ ተስማሚ የኾነ የአየር ንብረት ያላት እና የከተማዋ ሕዝብም ሰው ወዳድ ነው፡፡ ደሴ ውስጥ እንግዳ መከበር ብቻ ሳይኾን ይወደዳል፡፡ የአንዱ ዕምነት በሌላው ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ደሴዎች ፍቅራቸው አይጠገብም፡፡
በደሴ ከተማ ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ከከተማ አሥተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ደሴ ከተማ በቅርቡ ደግሞ ከ30 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት የሁለት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራዎች ጀምራለች፡፡
የደሴ ከተማ መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ተወካይ ኀላፊ ብርሃኑ ገበየሁ የኮሪደር ልማቱ እስከ ታኅሣሥ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የደሴ ከተማን ይበልጥ የሚያስውብ፣ ዘመናዊ ከተማ የሚያደርጋት፣ በሚለማው ኮሪደር ሰዎች በእግራቸው እና በብስክሌት እየተንቀሳቀሱ ጤናቸውን የሚጠብቁበት፣ በሚገነቡት መዝናኛ ሥፍራዎች አረፍ ብለው በማንበብ ዕውቀት የሚገበዩበት፣ ቀጥተኛ የኾነ እና ያልኾነ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት እንደሚኾንም አቶ ብርሃኑ ገልጸውልናል፡፡
በአይጠየፍ አዳራሹዋ፣ በጀሜ እና ጢጣ ተራሮቿ የምትታወቀው ደሴ ወይዘሮ ስኂን፣ እቴጌ መነን እና መምህር አካለወልድ (ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት) የመሳሰሉ የዕውቀት ተቋማትን ማልዳ የገነባችው ደሴ ከተማ ራሷን በተለያዩ ግንባታዎች ይበልጥ እያስዋበች ትገኛለች፡፡ በደሴ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ከተማዋ በተሻለ መልኩ የምትዋብ ሲኾን በቀጣይ በከተማዋ በሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ደግሞ ይበልጥ እንደምትዋብ አቶ ብርሃኑ ገልጸውልናል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!