“ሀገራዊ ህልም ዕውን እንዲኾን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የራሳቸውን ገንቢ ሚና መወጣት አለባቸው” አደም ፋራህ

38

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራዊ ህልም ዕውን እንዲኾን እንደሀገር ባስቀመጥናቸው የጋራ ህልም ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የራሳቸውን ገንቢ ሚና መወጣት አለባቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማሥተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት ካለባቸው ሕዝባዊ ኃላፊነት አኳያ የሀገር ህልም እንዲሳካ ከፍተኛ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በሚከታተሏቸውና በሚቆጣጠሯቸው ተቋማት እና በመራጭ ሕዝባቸው ውስጥ እንዲሠሩ ያስፈልጋል፤ ይህን መነሻ በማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ አስረድተዋል። ይህን የገለጹት በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች አመራሮች እየተሰጠ ባለው ሥልጠና ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ከፍታ የሚያደርሳትን እና ለትውልድ የሚሻገር ህልም ታልማለች፤ ይህ ህልም እውን ይሆን ዘንድም ምቹና ነባራዊ ኹኔታዎች አሏት ብለዋል አቶ አደም። በመሆኑም የሀገራችንን መበልፀግ እውን ለማድረግ የጋራ ህልም ሊኖረን የሚገባ ሲኾን፤ ህልማችን በረጅም ግዜ የሚሳካ በመሆኑ ህልማችን እውን ይሆን ዘንድ ኃላፊነታችንን በተገቢው ደረጃ መወጣት አለብን ሲሉ ገልጸዋል።

ህልምን ህያው ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ ትክክለኛ ሃሳብ መሆኑን የገለጹት ክቡር አቶ አደም የመደመር ሃሳብ ኢትዮጵያን ከማሻገር አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጭምር የሚተርፍ መኾኑንም አብራርተዋል። ሀገሪቱ ያላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ ከዓላማው ጎን የሚሰለፍ ሕዝብ እንዲሁም የተገነቡ ተቋማት የሀገራችንን ህልም ዕውን ለማድረግ አስቻይ ኹኔታዎች ከሚባሉት ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱ መሆኑን አስረድተዋል።

ህልም የጋራ መረዳትና ርዕይ ጋር የተገናኘ እንደኾነና በምናቅዳቸው ዕቅዶች፣ ልዩ ልዩ ስትራቴጂዎችና ከምንሠራቸው ሥራዎችና ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ አሳስበዋል። ህልም ከትላንት ይልቅ ዛሬ ላይ፣ ከዛሬ ይልቅ ደግሞ ነገ ላይ የሚያተኩር፣ አንዱ ትውልድ የሚጀምረው፣ ቀጣዩ ትውልድ የሚኖረው እንደኾነም ነው አቶ አደም የገለጹት።

የሀገሪቱ ህልም ዕውን የመሆን ትልቅ ተስፋ ከወዲሁ እየታየ መሆኑ፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በለውጡ ውስጥ የገጠሙንን ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ከፍተኛ ዕድገት እያሰመዘገበ መምጣቱን በተለይም ከባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንደኾነም ነው ያብራሩት፡፡

ቡናን ጨምሮ የሀገሪቱ የግብርና ምርቶች በዓለም እና በአፍሪካ የቀዳሚነት ደረጃን እየያዙ መምጣታቸው፣ ዓለምን ያስደነቀ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች መሠራቱ፣ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቁ መድረሱ፣ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደር ልማት መስፋፋት ማሳያዎች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ህልም ዕውን እንዲሆን በጋራ መሥራት እንደሚገባም አንስተው የአመራር ፅናት፣ ቁርጠኝነት፣ በመተማመን እና በትብብር መሥራት እንደሚገባም አደም ፋራህ አስገንዝበዋል ሲል የተወካዮች ምክር ቤት ድረ ገጽ አስነብቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከመኸር ሰብል ከ740 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ በደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ ገለጸ፡፡
Next articleየኮሪደር ልማቱ ውቧን ደሴ ይበልጥ ያስውባታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡