
ደሴ: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምርት ዘመኑ የተሻለ የዝናብ ሥርጭት በመኖሩ፣ የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሚገባ በመጠቀማቸው ብሎም የአረም እና ተባይ ቁጥጥር በማድረጋቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ የቃሉ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ አይሻ እንድሪስ እና አቶ መሐመድ ሰይድ የቃሉ ወረዳ 021 ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው ፡፡ አርሶ አደሮቹ በ2016/17 የመኸር እርሻ ማሽላ እና ጤፍ መዝራታቸውን ነው ለአሚኮ ያስረዱት፡፡ በዘንድሮው ዓመት የሰብሉ ቁመና የሚያስደስት መኾኑን እና የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡
በተለይ በባለፈው ዓመት በዝናብ እጥረት እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የምርት እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሮቹ በዘንድሮው የ2016/17 የመኸር እርሻ ግን የዝናብ ሥርጭቱ የተስተካከለ በመኾኑ፣ የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሚገባ በመጠቀማቸው እንዲሁም የአረም እና ተባይ ቁጥጥር በማድረጋቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ነው ያብራሩት፡፡
የቃሉ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ሀሰን ሰኢድ በወረዳው በ2016/17 የመኸር እርሻ ከ22 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን አተናግረዋል፡፡
በመኸር ከተዘሩ ሰብሎች ማሽላ፣ ጤፍ፣ ስንዴ እና ማሾ እንደሚገኙበት የተናገሩት አቶ ሀሰን ከዚህ ውስጥ ማሽላ 50 ከመቶ እንደሚሸፍንም ገልጸዋል፡፡
ምክትል ኀላፊው ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸው ወቅታዊ የሰብሉ ቁመና በእጅጉ አስደሳች እንደኾነ እና ከ740 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ነው ያብራሩት።
ዘጋቢ፡- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!