“የኮሪደር ልማቱ ጎንደርን ዳግም የሚያድስ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው

49

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ ከሚሠሩ የልማት ሥራዎች መካከል በፋሲል አብያተ መንግሥት ግቢ እና አካባቢው እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ይገኝበታል። የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን እድሜ እና ታሪክ በሚመጥን መንገድ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው ነግረውናል።

ሥራውን በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ላለፉት ሦስት ወራት በሌሊት ጭምር ሲሠራ ቆይቷል። በከተማ አሥተዳደሩ በኩል የሚጠበቀውንም ሥራ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ በክልሉ በተፈጠረው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ግብዓቶችን በወቅቱ ማቅረብ ባለመቻሉ አንዳንድ ሥራዎች ላይ መዘግየት መፈጠሩን አንስተዋል።

ግብዓቶችን በአጭር ጊዜ በማቅረብ እስከ ኅዳር 15/2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ በምዕራፍ አንድ የተያዘውን የኮሪደር ልማት ሥራ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በቀጣይ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ጎንደር ይበልጥ ደምቃ የምትታይበት ይኾናልም ነው ያሉት።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ለመጀመር ከአየር ማረፊያ እስከ ፒያሳ የሚደርስ የ12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የዲዛይ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

የዲዛይን ሥራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ሥራ የሚጀምር ይኾናል። ሥራው በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር፣ በፌዴራል እና በክልሉ መንግሥት ድጋፍ የሚሠራ ነው። በቀጣይ ደግሞ በከተማ አሥተዳደሩ ጭምር ለመሥራት በዕቅድ መቀመጡን ገልጸዋል። የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ማኅበረሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

የኮሪደር ልማቱ የሥራ ባሕልን፣ የዕውቀት እና የልምድ ሽግግር በማሳደግ አቅም ፈጥሯል። የኮሪደር ልማቱ አካል የኾኑ በመንገድ ዳር በሚተከሉ ስማርት ፖሎች የሚገጠሙ ካሜራዎችም ወንጀልን ለመከላከል አቅም ይኾናሉ። የከተማዋ የኮሪደር ልማት የከተማን ጽዳት እና ውበት በማስጠበቅ የማኅበረሰቡን የጤና ሁኔታ ለማሻሻልም ያግዛል።

በከተማ አሥተዳደሩ የተጀመሩ እና የታቀዱ ሥራዎች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገቡ በቀን ብቻ ተወስኖ የነበረውን የቅርሶች ጉብኝት በሌሊት ጭምር ለማከናወን ያግዛል። ይህም በጎንደር ከተማ እና አካባቢው ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።

የጎንደር የባሕል ማሳያ የኾኑ የአዝማሪ እና ባሕላዊ ቤቶች የአካባቢውን ባሕል ለማጉላት የበለጠ እድል እንደሚያገኙም ከንቲባው ጠቁመዋል።።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያን የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ግንባታ የሚደነቅ ነው” የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና ወታደራዊ አታሼዎች
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተለያዩ ሹመቶችን ሰጡ።