
ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ በፀጥታና ደኅንነት ረገድ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራና አስተማማኝ ተቋም ገንብታለች ሲሉ የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና ወታደራዊ አታሼዎች ተናግረዋል። በኢትዮጵያ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የመከላከያ ሚኒስትሮቹና አታሼዎቹ ከጉባዔው ተሳትፎ በተጨማሪ የኢትዮጵያን የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በዚህም በቢሾፍቱ የሚገኘውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንን ጎብኝተዋል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደርን፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትንም ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም የኢትዮጵያን የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ግንባታ የሚደነቅና በጥሩ ማሳያነት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም በሳይበር ደኅንነት፣ በፋይናንስ ደኅንነት፣ በመሰረተ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች የላቀ ቴክኖሎጂና የበቁ ባለሙያዎች እንዳሉ ተገንዝበናል ብለዋል። የኢትዮጵያ የጤና፣ የግብርና፣ የጸጥታና ደኅንነት፣ የሎጅስቲክ፣ የከተማ ልማትና ሌሎች ዘርፎችን በሰው ሠራሽ አስተውሎት ለመደገፍ የተጀመረው ጥረት አስደናቂ መሆኑን አንስተዋል።
የዛምቢያ መከላከያ ሚኒስትር፣ በኢትዮጵያ የጋና ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ፣ የዩጋንዳ የመከላከያ ሚኒስቴር የፖለቲካ ዘርፍ ኮሚሽነር፤ ኢትዮጵያ በጸጥታና ደህንነት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎትና ሌሎችም ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ አሠራሮችን በመዘርጋት በአህጉሪቱ በጥሩ ማሳያነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያና ደኅንነት ተቋም ጠንካራ መሰረት ያለው የአፍሪካም ኩራት መሆኑን በጉብኝታችን አረጋግጠናልም ነው ያሉት።
የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ፤ ኢትዮጵያ በጸጥታና ደኅንነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፎች እያከናወነች ያለውን ተሞክሮ ለአፍሪካውያን ማካፈሏን አንስተዋል። በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የመከላከያ ሚኒስትሮችም የኢትዮጵያን የተቋም ግንባታና ነባራዊ ሁኔታ በማድነቅ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው በአዲስ አበባው ታሪካዊ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ በፓን አፍሪካ ጽንሰ ሃሳብ፤ አፍሪካዊ የሰላምና ጸጥታ ተቋም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል። በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ላለፉት ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በነበረው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ በአህጉሪቱ ሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር ተጠናቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!