
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን ብልጽግና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ነገን የሚዋጁ ታዳጊዎችን ማፍራት ላይ በትብብር መሥራት ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አሳሰቡ። የአብርኾት ቤተ መጻሐፍት ከአቦጊዳ ሮቦቲክስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ጋር በመተባበር በሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ላሰለጠናቸው ታዳጊዎች ዕውቅና ሰጥቷል። ከዕውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብሩ ጎን ለጎንም ኢግዚቢሽንም ተካሂዷል።
በዚሁ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ኢትዮጵያ ባለመፍጠር እና በተረጂነት ለረጅም ዘመናት የምትታወቅ መኾኗን አንስተዋል። የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች በፈጠራ እና ምርምር የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና እውን የማድረግ ጥረት መጀመሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ነገን የሚዋጁ ታዳጊዎችን ማፍራት ላይ በትብብር መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ታዳጊ ወጣቶች በመፍጠር፣ በመመራመር እና ቴክኖሎጂ መር የኾኑ ተግባራትን በትኩረት በመሥራት ለሀገር እድገት እና ለዜጎች ተጠቃሚነት የሚያደርጉትን ጥረት ሊቀጠሉ ይግባልም ብለዋል።
ለዚህ ስኬት ደግሞ ቤተሰብ እና ሀገር አጠቃላይ ዜጎች በትውልድ ላይ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ መስኮች የሚፈለገውን ስኬት እና ውጤት ለማምጣት የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ መኾኑን ጠቅስው፤ ለዚህም በክህሎት እና እውቀት የተካኑ ታደጊዎችን ማፍራት ይገባል ብለዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የኮዲንግ ስልጠና ዕድል የተመቻቸ መኾኑን ጠቅሰው እስካሁን ዕድሉን ያልተጠቀሙ ሁሉ ስልጠናውን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
