
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ያለንበት ዓለም አቀፋዊ አውድ የፓን አፍሪካ የመከላከያ ኃይሎችን ትብብር እውን የሚያደርግ ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ተግባር መግባትን የግድ እንደሚል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ። የመጀመሪያው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ከጥቅምት ከ05/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጉባዔው ላይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በአፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች መካከል ያለውን ትብብር የተመለከተ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል። ባቀረቡት ገለፃ “ዓለም በአሁኑ ወቅት አንዱ ሌላውን ጥሎ የሚያልፍበት የበይ እና ተበይ አውድ ውስጥ ይገኛል” ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ ዓለም አቀፋዊ አውድ ውስጥ አፍሪካ አንድነቷን ካላጠናከረች ልክ እንደ በፊቱ የሌሎች የመጫወቻ ሜዳ የመኾን ዕጣ እንደሚገጥማትም ነው ያነሱት።
ቀደምት አባቶቻችን በየጊዜው በሁሉም መስክ የሚያጋጥሙ የደኅንነት ስጋቶችን የሚመክት አንድ ወጥ የአፍሪካ የመከላከያ ኃይል እንደሚያስፈልግ ቀድመው መናገራቸውንም አምባሳደር ሬድዋን አውስተዋል። ከብዙ አስርት ዓመታት በኋላ አፍሪካ ቀደምት አባቶች ያስቀመጡትን ራዕይ አሳክታለች ወይ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።
አህጉሪቱ በአሁኑ ወቅት በርካታ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እየተጋፈጠች ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን አሸባሪዎች፣ ጽንፈኛ ቡድኖች፣ የባሕር ላይ ወንበዴዎች እና የድንበር ግጭቶች እያመሷት መኾኑን ገልጸዋል። የውጭ ኃይሎችም በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ አህጉራዊ የደኅንነት ስጋት መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
“አፍሪካ እያጋጠሟት ያሉትን ችግሮች የውጭ ኃይሎች እንዲፈቱላት ማማተር አይገባትም” ያሉት ጀኔራል ዳይሬክተር ሬድዋን ሁሴን ከውጭ የሚመጣ መፍትሔ ቢኖር እርስ በርስ እየተጋጨን ልዩነቶቻችንን አስፍተን በችግር እንድንማቅቅ የሚያደርግ ነው ብለዋል። የችግሩ መፍቻ ቁልፍ በእጃችን በመኾኑ ራሳችንን ችለን መቆምና አንዳችን ሌላውን በማገዝ ወደተሻለ አህጉራዊ ግብ መጓዝ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
እያንዳንዱ ሀገር የራሱን ችግር ለመቅረፍ የሚያደርገው ጥረት፣ ማኅበራዊ ፍትሕን እና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት የውስጥ ግጭቶችን በመፍታት ኹኔታዎችን እንደሚያረግብ ጠቁመዋል። መተማመን ላይ የተመሠረተ የሀገራት ግንኙነት፣ ችግሮችን በሰላማዊ ድርድር የመፍታት ባሕል፣ የተፈጥሮ ሃብቶችን በፍትሐዊነት መጠቀም ግጭቶችን አስወግዶ አፍሪካዊ የጋራ የብልጽግና እና የሰላም ራዕይን እንደሚያሳካም ተናግረዋል።
በአፍሪካ የሚከሰቱ አካባቢያዊና ውጫዊ የፀጥታና ደኅንነት ችግሮችን የትኛውም ሀገር ብቻውን እንደማይወጣቸው ጠቅሰው፤ ጠንካራ ፓን አፍሪካዊ ወታደራዊና የደኅንነት ትብብር ወሳኝ መኾኑን አብራርተዋል። አምባሳደር ሬድዋን ፓን አፍሪካዊ የቴክኖሎጂና ወታደራዊ መሳሪያዎች ምርት፣ የወታደራዊ ሥልጠና፣ አቅም ግንባታ፣ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ፣ ወቅቱን የጠበቀ የደኅንነት መረጃ ልውውጥ እና የባሕር ኃይል ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ወታደራዊ ትብብር እንዲጎለብት አበክራ እየሠራች መኾኗን ጠቅሰዋል። ለአብነትም በወታደራዊ ልዩ ልዩ መስኮች የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ መኮንኖችንና ሙያተኞችን ከማሠልጠን ባለፈ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገች እንደምትገኝ ነው ያብራሩት። አፍሪካውያን ከውጭ በሚገቡ ወታደራዊ መሳሪያዎች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት እንዲያላቅቁም የራስን አህጉራዊ አቅም መገንባት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ በጋፋትና ሆሚቾ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች የጀመረቻቸውን ተምሳሌታዊ ተግባር በተሞክሮነት አንስተው፤ አህጉራዊ የወታደራዊ ቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ትብብር አስፈላጊ ነው ብለዋል። የፓን አፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ስትራቴጂን መቅረፅ ወሳኝ እንደኾነ ገልጸው፤ ተቋማዊ ማዕቀፍ መፍጠር፣ ፓን አፍሪካዊ ማኅበረ ፖለቲካዊ ግንኙነትን ማጠናከር፣ ሕጋዊ ሂደቶችን መጀመር፣ የሁለትዮሽና የብዝኀ ዘርፍ ወታደራዊ ግንኙነቶችን አህጉራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የፓን አፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ስትራቴጂ የአህጉሪቱን የፀጥታ እና ደኅንነት ሥራዎች ለመምራት አንድ ወጥ ፍኖተ ካርታ እንደሚያገለግል ጠቅሰው ሀገራት ከአህጉራዊ ግቦች የተናበበ ፖሊሲ እንዲኖራቸውም ጠይቀዋል። የኢዜአ ዘገባ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ወታደራዊ ትብብር እውን መኾን መሠረት የሚጥሉ ግንኙነቶችን በየቀጣናው እያካሄደች እንደምትገኝም ተናግረዋል።
አህጉራዊ ትብብርን እውን ለማድረግ በሁሉም ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ግንኙነትን ማዳበር እና መሪዎች የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
