
አዲስ አበባ: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ ሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሻምበል አብርሃም ሳቃታ አመለካከታችን መስመር ካልያዘ ለታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶችም መግቢያ ክፍተት እየፈጠርን እንደኾነ መገንዘብ ያሽፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያዊነት የተሸመነበትን ጥልቅ ትርጉም እና ድንቅ ጥበብ በውል ያልተረዱ አካላት መለያየትን እና ግላዊነትን ለዘመናት ቢሰብኩም መሠረተ ጽኑ የኾነው ኢትዮጵያዊነት አሁንም ሕያው ኾኖ ይቀጥላል ሲሉም አብራርተዋል።
ሻምበል አብርሃም ኢትዮጵያውያን በጥቃቅን ጉዳዮች እየተደናገርን ለእራሳችን ችግር ከምንፈጥር ትናንት አብረው ያቆዩንን የወል ትርክቶችን በማጠናከር ዛሬን አልፈን ነገን ለማየት መትጋት ይገባል ብለዋል። “የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምሳሌው ሰርገኛ ጤፍ ነው” የሚሉት ሻምበል አብርሃም አንድነታችን በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ቢታሰስ ስብጥሩ የሚደንቅ እና አክብረን ልናጠናክረው የሚገባ ሃብታችን ነው ሲሉ ነው የተናገሩት።
ለእኔ ብቻ የሚለው የስግብግብነት መገለጫ ባህሪ አንድነታችንን በመናድ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ክፍተትን የሚፈጥር እና ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል አካሄድ በመኾኑ ጥንቃቄ እናድርግ ሲሉም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት። ስማችን ኢትዮጵያውያን፤ ታሪካችን ባለዝና እና የወል ሀገር እንዲሁም ትርክታችን ኢትዮጵያ መኾኑን በመገንዘብ ለእኛ ስለኛ በጋራ ልንቆም ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
