በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉ ተገለጸ።

19

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከውጭ የሚገቡ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ። መንግሥት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው።

ንቅናቄው የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም የማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ ነው። የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ተጨባጭ አስተዋፅኦ ወደ ማበርከት እየተሸጋገረ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራም ትልቅ ሚና እየተጫወተ መኾኑን ገልጸዋል። የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ፣ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ሀገራዊ ወጪን መቀነስ ላይም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

ንቅናቄው ባለፈው ዓመት ብቻ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን አመልክተዋል። ለዘርፉ የሚቀርቡ የብድር፣ የውጭ ምንዛሪ እና የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰው፥ በዚህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በተያዘው ዓመትም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ሚኒስትሩ ያረጋገጡት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ማኅበራዊ ኀላፊነት አለብኝ ማለት ይጠበቅበታል” ነገሠ በላይ (ዶ.ር)
Next article“ግለሰባዊ ትርክቶችን በመተው የኢትዮጵያዊነት ውልን በሚያጎለብቱ የጋራ ታሪኮቻችን ላይ ማተኮር ይገባል” የቀድሞ ሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሻምበል አብርሃም ሳቃታ