“የወል ትርክትን በመገንባት ጊዜያዊ ፈተናዎችን መሻገርና ሀገራዊ ለውጡን ለማጽናት ዜጎች በጋራ ሊቆሙ ይገባል” አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

41

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የሀሳብና የተግባር አንድነትን በማቀናጀት ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን በላቀ ትጋት ማከናወን እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል። ”የህልም ጉልበት ለእመርታዊ ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪዎችና አባላት የሥልጠና መድረክ እየተካሄደ ነው።

የሥልጠናው ዓላማ በሀገራዊ ለውጡ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና የሚያጋጥሙ ችግሮችን የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ለመፍትሔው ለመሥራት መሆኑ ተገልጿል። በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ የሀሳብና የተግባር አንድነትን በማቀናጀት ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሥራዎችን በውጤታማነት ማከናወን ይገባል ብለዋል።

የምክር ቤት አባላት በለውጥ ወቅት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል ለመሻገር የችግሩ መነሻ ላይ የጋራ መግባባት መያዝና ለመፍትሔውም መትጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠንከር የወል ትርክትን በመገንባት ጊዜያዊ ፈተናዎችን መሻገርና ሀገራዊ ለውጡን ለማጽናት ዜጎች በጋራ ሊቆሙ ይገባል ነው ያሉት።

የምክር ቤት መሪዎችና አባላት የሥልጠና መድረክም የሀሳብና የተግባር አንድነትን በማቀናጀት ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን በላቀ ትጋት ለማከናወን ይበልጥ መነሳሳትን ለመፍጠር ነው ብለዋል። ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችን በአግባቡ በመረዳት በሕገ-መንግሥቱ የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራና ኃላፊነት በላቀ ብቃት ለመወጣት መሆኑንም አፈ-ጉባዔው አንስተዋል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ.ር)፤ የሥልጠናው ዓላማ የምክር ቤት አባላት ሀገራዊ ህልሞችን ለማሳካት በተሄደበት እርቀት ልክ የተገኙ ድሎችና ያጋጠሙ ፈተናዎችን በአግባቡ እንዲገነዘቡ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። ኢዜአ እንደዘገበው በለውጡ ሂደት የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል ለችግሮች ደግሞ የጋራ መፍትሔ እየሰጡ ለመቀጠል በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተሟላ ግንዛቤ መያዝ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

የምክር ቤት መሪዎችና አባላት ሥልጠና በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በውጭ ግንኙነት፣ በተቋም ግንባታና የአመራር ብቃት ላይ በማተኮር ለዘጠኝ ቀናት የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም” የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ
Next article“ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ማኅበራዊ ኀላፊነት አለብኝ ማለት ይጠበቅበታል” ነገሠ በላይ (ዶ.ር)