
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በየጊዜው በመጤ ተምች፣ በበርሃ አንበጣ እና ተዛማች ተባዮች ሲፈተን ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኙ ሁለት ዞኖች የግሪሳ ወፍ ተከስቶ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንዳሉት በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞን አራት ወረዳዎች በሚገኙ 8 ቀበሌዎች ከመስከረም 22/2017 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የግሪሳ ወፍ ተከስቷል።
የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ በአውሮፕላን ርጭት ለመከላከል ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ቀርቧል። ኮምቦልቻ እና ሸዋሮቢት የሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያ ቦታዎችን የማዘጋጀት ሥራም እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በቅርብ ቀንም ርጭት ይደረጋል ነው ያሉት። ለአውሮፕላን ርጭት እንዲያመች የግሪሳውን ወፍ ማደሪያ እና ሌሎች ሥራዎችን በ”ጅፒኤስ ኮኦርዲኔት” በባለሙያ የመለየት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
ርጭቱ እስኪጀምር ድረስ አርሶ አደሮች በባሕላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል። በግሪሳ ወፍ የደረሰውን ጉዳትም በቀጣይ በጥናት ተለይቶ የሚቀርብ ይኾናል። የግሪሳ ወፍ ብቻ ሳይኾን የአንበጣ መንጋ እንዳይከሰት የማሳ አሰሳ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ከተከሰተም በፍጥነት ለተቋሙ እንዲያሳውቁ ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የግሪሳ ወፍ እና የአንበጣ መንጋ የክብደታቸውን ያህል የሚመገቡ በመኾኑ የሚያደርሱት የጉዳት መጠን ከፍተኛ ነው። 2 ሚሊዮን የግሪሳ ወፍ በአንድ አካባቢ ቢከሰት በቀን 50 ቶን እህል የማውደም አቅም አለው። ሁለቱም ብዙ ቦታ ላይ በመድረስ ያመሳስላቸዋል። የግሪሳ ወፍ በቀን እስከ 64 ኪሎ ሜትር፣ አንበጣ ደግሞ በቀን የንፋስን አቅጣጫ ተከትሎ እስከ 100 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ጉዳት የማድረስ አቅም አላቸው።
በተለይም ደግሞ የግሪሳ ወፍ በ12 ቀናት ውስጥ እንቁላል በመፈልፈል ለመብላት የሚደርስ ነው። የግሪሳ ወፍ የአፍሪካ በተለይም ደግሞ ከሰሃራ በርሃ በታች ያሉ ሀገራት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ችግር እንደኾነም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
