
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለማችን 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ድህነት ውስጥ የሚገኙ መሆኑን እና ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጉት ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ መኾናቸውን የዓለም የልማት ፕሮግራም በድረ ገጹ ላይ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የዓለም የልማት ፕሮግራም ዛሬ ይፋ ያደረገው የድህነት ደረጃን የተመለከተ ሪፖርት 455 ሚሊዮን የሚኾኑት በድህነት ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ግጭቶች ባሉበት አካባቢ የሚኖሩ መሆናቸውን ነው። በ112 ሀገራት በ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሰዎች ላይ ተመሥርቶ በተደረገ ጥናት 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከድህነት ጋር እየታገሉ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያትታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግጭቶች እና ጦርነቶች መጨመራቸውን እና ከምንጊዜውም በላይ ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የልማት ፕሮግራሙ አሳውቋል።
በሪፖርቱ 584 ሚሊዮን የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የኾኑ ታዳጊዎች በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸው ተጠቅሷል። በግጭት ቀጣናዎች ያሉ ታዳጊዎች የሞት ምጣኔያቸው ስምንት በመቶ መሆኑን እና ሰላማዊ በኾነ አካባቢ የሚኖሩት ደግሞ 1 ነጥብ 1 በመቶ የሞት ምጣኔ እንዳላቸውም ተገልጿል።
በዓለማችን 83 ነጥብ 2 በመቶ የሚኾኑት ድሃ ሕዝቦች የሚኖሩት በሰብ ሰሃራ የአፍሪካ አካባቢዎች እና በደቡባዊ እስያ እንደሆነ ሪፖርቱ ጠቁሟል። ሪፖርቱ ሲጠናቀር የድህነት ወለል መለኪያ አድርጎ የተጠቀመው የመጠለያ፣ የንፅሕና መጠበቂያ፣ የኤሌክትሪክ፣ የማብሰያ ኃይል አማራጭ፣ የምግብ እና የትምህርት መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
