
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለወትሮም ቢኾን ውብ የኾነችውን ባሕርዳር ይበልጥ ውብ የማድረግ ተግባሩ በኮሪደር ልማት ተጀምሯል። ይህ የባሕርዳርን ውበት የሚገልጠው የኮሪደር ልማት በውስጡ በርካታ ለቱሪስትም ኾነ ለአካቢው ነዋሪዎች የሚኾኑ ነገሮችን አቅፎ ይዟል፡፡
ባሕርዳር የምትታወቅበትን ብስክሌት ከቆየበት የተቀዛቀዘ ኹኔታ አውጥቶ ይበልጥ ለከተማዋ መገለጫ ለማድረግ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በኮሪደር ልማቱ በኩል ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ የኮሪደር ልማት በሚሠራበት ወቅት በመንገዱ ግራ እና ቀኝ በኩል ለብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አድርጎ ለመሥራት ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ እንደኾነ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ይገልጻል፡፡
ባሕር ዳር ቀደም ብሎ በብስክሌት ትታወቅ እንደነበር የሚናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ይህም ለከተማዋ አንዱ ገጽታዋ (መታወቂያዋ) እንደነበር ነው የሚገልጹት፡፡ ብስክሌት ለረጅም ጊዜ በባሕርዳር ጎዳናዎች ላይ ያሽከረክሩ የነበሩት እነዚህ ነዋሪዎች አኹን ላይ ለብስክሌት የተመቸ የመንገድም ኾነ በሌሎች ጉዳዮች ምክንያት ብስክሌታቸውን ቤት እንዲያስቀምጡ መገደዳቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ነዋሪዎቹ አኹን ላይ በከተማው ውስጥ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ብስክሌታቸውን ከተቀመጠበት ቦታ አንስተው ለመዝናናትም ኾነ ሌሎች ሥራዎችን ለመከወን ሊጠቅማቸው እንደሚችልም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡ ለመኾኑ የባሕርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ምን ያክል ለብስክሌት መጓጓዣ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ይኾን?
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የኮሪደር ልማቱን አስመልክተው እንዳሉት የኮሪደር ልማቱ በአጠቃላይ የባሕርዳርን ውበት ለመግለጥ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ይህ ሥራ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲኾን በዚህ ሥራ የባሕርዳር መገለጫ የኾነውን ብስክሌት ታሳቢ ያደረገ ሁለገብ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ነው ያብራሩት፡፡
የመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ከ3 እስከ 2 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ዲዛይኑ ተጠናቆ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ 50 ሜትር ያላነሰ ስፋት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት ከመንገዱ ዳር ጀምሮ አራት ሜትር የአረንጓዴ ልማት፣ ሦስት ሜትር የብስክሌት እና አምስት ሜትር ደግሞ የእግረኛ መንገድ እንዲይዝ ተደርጎ ሥራው ስለመጀመሩ ነው ያመላከቱት፡፡
በዚህ ሥራ ውስጥ የሕዝብ ማረፊያዎች፣ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የተለያዩ ትኩስ ምግቦች መሸጫዎችን የሚያካትት እንዲኾን ተደርጎ ስለመሠራቱ ነው ያስረዱት፡፡ ብስክሌት የባሕርዳር መገለጫ እና ባሕሏ ነው የሚሉት ምክትል ከንቲባው በብስክሌት ስመ ጥር የኾኑ ስፖርተኞችን ያፈራች ከተማም ስለመኾኗ አውስተዋል።
ባሕርዳር ከዚህ በፊት የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮናን በማዘጋጀትም የምትታወቅ ከተማ እንደኾነች ገልጸው ይህን ስሟን አጉልቶ የሚያወጣ እና የብስክሌት አብዮትን የሚመልስ ሥራ ከኮሪደር ልማቱ እንደሚጠበቅም ነው ያብራሩት፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ የብስክሌት ፓርኪንግ እንደሚኖር እና ይህም ብስክሌት መጋለብ ለሚፈልግ ሁሉ እዚሁ ፓርክ መከራየት አሊያም ብስክሌት ያለው አስቀምጦ በፈለገው ጊዜ መጠቀም እንዲችል የሚያስችል ሥራ ለመሥራትም ታሳቢ ስለመደረጉ ነው የገለጹት፡፡
ምክትል ከንቲባው ማንኛውም ሰው ልክ እንደሠለጠኑት ሀገራት በፈለገው ቦታ ክፍያ ከፍሎ በብስክሌት የፈለገበት ቦታ ደርሶ በደረሰበት ማስቀመጥ የሚችልበት አሠራር እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡ ይህም ሥራው ሲያልቅ በኢንተርፕራይዝ ደረጃ የሚሠራ እንደኾነ ነው ያመላከቱት፡፡ በዚህ የከተማዋን ገጽታ በሚለውጥ ሥራ ላይ ለከተማዋ የሚያስቡ ባለሃብቶችም ኾኑ ሌሎች ግለሰቦች እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚኾነው የኮሪደር ልማት ላይ ያሉ ለብስክሌት ምቹ የኾኑ መንገዶችም የብስክሌትን አብዮት ይመልሳሉ ብለው እንደሚያስቡም ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
