ለባሕር ዳር ልዩ ገጽታ የሚያላብሰው የጣና ተስፋ ኮሪደር ልማት።

86

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕርዳር ካሏት የውበት እና የቱሪስት መስህብ ውስጥ የጣና ሐይቅ የፊት መስመሩን ይይዛል፡፡ ከተማዋ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው የጣና ሐይቅ ነው፡፡ ይህን የከተማዋን ጌጥ ይበልጥ ለከተማዋ ውበት እንዲያላብስ የመግለጽ ሥራ የኾነው የኮሪደር ልማት ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ይህ የባሕርዳር ውበት የኾነውን ጣናን የሚገልጠው የኮሪደር ልማት ለቱሪስትም ኾነ ለአካቢው ምቹ ኹኔታዎችን የሚፈጥር ሥራም ነው፡፡ ጣና በግልጽ እንዲታይ እና በውስጡ ያሉት እንደ ብርቅየ አዋፋት እና የጣና ጀልባዎችን በውኃው ላይ እንደፈለጋቸው ሲንሳፈፉ ለማየት ብሎም በርቀት የሚታዩትን ደሴቶቿን ለመግለጥ ታሳቢ ያደረገው የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው፡፡

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የኮሪደር ልማቱን አስመልክተው እንዳሉት የኮሪደር ልማቱ በአጠቃላይ የባሕርዳርን ውበት ለመግለጥ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ይህ ሥራ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲኾን በዚህ ሥራ የባሕርዳር መገለጫ የኾነውን የጣናን ሐይቅ ውበት መግለጽ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ከ3 እስከ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ዲዛይኑ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ 50 ሜትር ያላነሰ ስፋት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት ከመንገዱ ዳር ጀምሮ አራት ሜትር የአረንጓዴ ልማት፣ 3 ሜትር የብስክሌት እና 5 ሜትር ደግሞ የእግረኛ መንገድ እንዲይዝ ተደርጎ ሥራው ስለመጀመሩ ነው ያመላከቱት፡፡

በዚህ ሥራ ውስጥ የሕዝብ ማረፊያዎች፣ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የተለያዩ የሕዝብ መዝናኛዋች የሚያካትት እንዲኾን ተደርጎ ስለመሠራቱም ነው ያስረዱት፡፡ በባሕርዳር የኮሪደር ልማት ተደብቆ የቆየውን የጣናን ውበት እንዲገለጥ በማድረግ ሥራው ይሠራል ነው ያሉት፡፡ አኹን ላይ ጣና በተለያዩ ነገሮች ከመንገዱ ጋር እንዳይናበብ ተከልሎ እንዳለ የገለጹት ምክትል ከንቲባው ጣናን ከመንገዱ ጋር እንዲናበብ ማድረግ የመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ሥራ እንደሚኾን ነው ያመላከቱት፡፡

ምክትል ከንቲባው አስሜ እንዳሉት አኹን ላይ መንገዱን ተከትሎ ለሚሄድ ሰው ጣናን የማየት ዕድሉ ጠባብ እንደኾነ እና ይህም በዛፍ አለያም በግንባታ የተከበበ ስለኸነ ነው ብለዋል። ይህን ጣናን ገለጥ የማድረግ ሥራው የሚጀምረው ዲፖ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ ስለመኾኑ ገልጸው ከተማ አሥተዳደሩ ከሠራው መዝናኛ ጋር በማናበብ እና ከዛም ቀጥሎ ከአባንቲ ቀጥሎ ያለው ቦታ በኮሪደር ልማቱ እንዲሠራ የሚደረግ ሲኾን ይህም ጣናን ይገልጣል ነው ያሉት፡፡

ሌላው የኮሪደር ልማት አካል በመኾን ጣናን የሚገልጠው በድሮው ሕዳር 11 እየተባለ የሚጠራው እና አሁን ዘንባባ መናፈሻ ተብሎ የሚጠራው ስፍራ እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡ በጣና ሐይቅ ትራንስፖርት እና በግዮን ሆቴል መሐል ያለው ሥፍራ እና ማንጎ መናፈሻ የሚባለውን ክፍት በማድረግ ጣናን መግለጥ ሌላው የኮሪደር ልማቱ ሥራ ነው፡፡

በጊዮርጊስ እና በአልማ መካከል ባለው ስፍራ ደግሞ ጣናን በመግለጥ ትልቅ የሕዝብ የመዝናኛ ስፍራ ማድረግ ሌላው ሥራ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል፡፡ በርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት እና በአልማ መካከል በሙን ላይት እና በኩሪፍቱ መካከል፣ በሹማቦ መናፈሻ አካባቢ ያለውን ሥፍራ ጣናን ክፍት የሚያደርግ የኮሪደር ልማቱ ሥራ ስለመኾኑ ነው ያብራሩት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ 17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እየተሠራ ነው።
Next articleየባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የከንፈር እና የላንቃ ክፍተት ላለባቸው ሕፃናት ነፃ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ገለጸ።