በኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ 17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እየተሠራ ነው።

106

ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሲሳይ አየለ በከተማዋ በሦስት ዙር የሚለማ 17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም 500 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ የሚመለከታቸዉ አካላት ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ጥናት በማድረግና የቦታ ልየታ በማካሄድ ከኮምቦልቻ ዩኒቨርሲቲ እስከ አደባባይ፣ ከአደባባይ እስከ ኮስፒ ደሴ መዉጫ እና ከልዑል መኮንን መገንጠያ እስከ አየር መንገድ ድረስ በሦስት ዙር ለማልማት ሥራ መጀመራቸዉን ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያዉ ዙር ሥራ 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ከተጀመረው ሥራ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚኾነዉ በሩብ ዓመቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ተጠናቅቆ በሥራ ላይ የዋለዉ መንገድ በታሰበለት ጊዜ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ መጠናቀቁን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ የአረንጓዴ ሽፋንን በማሳደግ፣ የተጨማሪ እግረኛ መንገድ በመፍጠር፣ የመዝናኛ ቦታዎችን በማዘጋጀት እና የመንገድ መብራትን በማሟላት የከተማዋን ዉበት ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከ17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩ የኮሪደር ልማት ጎን ለጎን በ102 ሚሊዮን ብር በጀት የመንገድ መብራት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ሥራ አሥኪያጁ ተናግረዋል ፡፡

የአንደኛ ዙር ቀሪ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በሥራ ላይ እንደኾነም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሥራ ላይ በዘርፉ ለተመረቁ አምስት የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏልም ነዉ ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ80 ሺህ ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሃብት መቀየር መቻሉን የአዲስ አበባ ጽዳት አሥተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
Next articleለባሕር ዳር ልዩ ገጽታ የሚያላብሰው የጣና ተስፋ ኮሪደር ልማት።