ከ80 ሺህ ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሃብት መቀየር መቻሉን የአዲስ አበባ ጽዳት አሥተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።

52

አዲስ አበባ: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኤጀንሲው “ደረቅ ቆሻሻ ሃብት ነው” በሚል መሪ ሃሳብ አውደ ርዕይ እና የግንዛቤ ፈጠራ መድረክ እያካሄደ ነው። የአዲስ አበባ ጽዳት አሥተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ.ር) አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና ጽዱ ለማድረግ ባለፉት አራት ዓመታት ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

በዚህም ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ወደ ሃብት የመቀየር ሂደት ከ1 ሺህ በላይ ለኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል። በ2016 ዓ.ም ብቻም ከ80 ሺህ ቶን በላይ ቆሻሻን ወደ ሃብት በመቀየር ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ማኅበረሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱን በአግባቡ እና በጥንቃቄ እንዲያስወግድ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ከቆሻሻ ነፃ የኾነች ከተማን እውን ለማድረግ በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል። የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ድኤታ ፋንታ ደጀን የኢትዮጵያ ከተሞች የአዲስ አበባን ተሞክሮ እንዲወስዱ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ለተተኪው ትውልድ ውብ እና ጽዱ፤ ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማን ለማስረከብ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የሊዋይ (LIWAY) ተወካይ ዓለምፀሐይ እጅጉ 250 ሺህ ለሚኾኑ ወጣቶች በተለያዩ የሙያ መስኮች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ በማስተባበር ተቋሙ ፕሮግራም ቀርጾ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች፣ አርቲስቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል። የደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ምርት አምርተው ወደ ገበያው የተቀላቀሉ ሥራ ፈጣሪዎችም ሥራዎቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል። አውደ ርዕዩ በግዮን ሆቴል አስከ ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም እንደሚቆይም ተገልጿል።

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“75ኛውን ዓለም አቀፍ የጠፈር ተመራማሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያን በዘርፉ ቀዳሚ እና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር እንጠቀምበታለን” ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ.ር)
Next articleበኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ 17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እየተሠራ ነው።