
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአሥተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር መለሰ አበበ በየወቅቱ በሚፈጠሩ ተፅዕኖዎች የማይናወጡ ተቋማትን መገንባት መቻል የተረጋጋ ሀገርን ለመፍጠር ቁልፍ መንገድ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የተቀዳጁ፣ ግዙፉ ምጣኔ ሃብታዊ አቅም የገነቡ፣ በሁሉም ዘርፍ የአስተማማኝ ኃይል ባለቤቶች፣ የዓለም የኃይል ሚዛን ወሳኞቹ ሀገራት እዚህ ለመድረሳቸው አስቀድመው በቁርጠኝነት እና ፅናት የገነቧቸው ተቋማት መሠረት ተደርገው ይነሳሉ።
ተቋማት መሠረተ ጽኑ፣ ዘመንን ተሻጋሪ፣ በግለሰቦች ይሁንታ የማይለዋወጡ፣ ነጻ እና ገለልተኛ፣ በእውቀት እና መርህ የሚመሩ ሲኾን ለአንድ ሀገር ፋይዳቸው የጎላ ነው። በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአሥተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና የቢዝነስ ልማት አገልግሎት አማካሪው መለሰ አበበ ተቋማት ሲገነቡ ዘመኑን የዋጁ እና ቀጣዩን ትውልድ ያገናዘቡ መኾን ይገባቸዋል ይላሉ።
ተቋማት ምንም ዓይነት የሂደት መለዋወጥ ቢኖር እንኳን ጸንተው የሚቆዩ ኾነው መገንባት አለባቸው ብለዋል። ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ ሀገራት ላይ የሚስተዋለው ችግር ተሳካላቸው የሚባሉ ተቋማት ሥርዓት ሲቀያየር እና ግለሰቦች ሲለዋወጡ ተቋማቱም ሲዳከሙ እና ሲወድቁ መስተዋሉ ነው ብለዋል መምህር መለሰ።
የዚህ ዓይነት ችግር የሚከሰተው በዋናነት ተቋማት በመዋቅር እና ሥርዓት መመራት አለመቻላቸው እንደኾነም ነው የሚያነሱት። በመኾኑም ጠንካራ እና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን ለመገንባት ነጻ፣ ገለልተኛ እና የተፈረሙ ሰነዶችን ማክበር፣ በተግባር መፈፀምም ተገቢ ስለመኾኑ ተጠቁሟል።
“እኛ ሀገር የሰነድ ችግር የለም፤ ነገር ግን ለቃል ታምኖ በቅንነት በተግባር የመፈፀም ቁርጠኝነት ይጎላል” ነው ያሉት።
ለሀገር እና ሕዝብ የሚበጁ፤ ቀጣይነታቸው የማያጠራጥር ተቋማት ሲገነቡ ፖለቲካዊ መረጋጋት እንዲሰፍን ያደርጋሉ ብለዋል። ዜጎች መረጋጋት ውስጥ ካሉ ፈርጣማ ኢኮኖሚ ያላትን ሀገር መገንባት እንደሚቻልም አንስተዋል። የተቋም ግንባታ ላይ አተኩሮ መሥራት የመጨረሻው ውጤት ለዜጎች ምቹ እና በምንም የማትናወጥ ሀገርን መገንባት እንደኾነም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡- ዮናስ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
