
ባሕር ዳር: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ተማሪ ሂትራ ደምሴ በቃሉ ወረዳ በገርባ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ከክፍል ክፍል የምታልፈው 1ኛ ደረጃን በመያዝ ነው፡፡ የሒሳብ ትምህርትን አብዝታ ትወዳለች። አድጋም የመድኃኒት ቅመማ ሳይንቲስት መኾን ትፈልጋለች፡፡
ሂትራ በቀለም ትምህርት ብቻ ሳይኾን በሥነ ምግባርም ጎበዝ መኾኗን ነው መምህሮቿ የመሰከሩላት፡፡ ጠንክሮ ማንበብን የምትወደው ሂትራ ወላጅ እና መምህራን የሚመክሩትን መተግበር እንደሚጠቅም ታምናለች፡፡
ደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብታ መማርም ትፈልጋለች፡፡ ለሁሉም ነገር ግን ወላጆች፣ መምህራን እና ታላቆች የሚመክሩትን መስማት ጥሩ ነውም ትላለች፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ነዋሪ እና በእስልምና ሃይማኖት የሀዲስ መምህር ሀጂ ሙሐመድ ጀውሐር አሕመድም በእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ሀዲስ እና ፍቂህን ከሥነ ምግባር አዋህደው ተምረው አድገዋል። ግብረ ገብነት በሰዎች ሕይዎት ላይ ቁልፍ መሣሪያ መኾኑንም ያነሳሉ፡፡
ሃይማኖት እና ሥነ ምግባር ተምሬ እንዳድግ ከጎንደር ወደ ወሎ በአደራ ተሰጠሁ የሚሉት ሐጂ ሙሐመድ ሃይማኖቴ እንዳስተማረኝ ታላላቆቼን አክብሬ፣ በሁሉም ነገር እያገለገልኩ እነሱም እየመረቁኝ እና ዱኣ እያደረጉልኝ ነው ያደግሁት ይላሉ፡፡ ሐጂ የሃይማኖት እና የሥነ ምግባር ስብዕናቸውን ሳይለፉ ሳይደክሙ በገንዘብ አልገዙትም፡፡ ተማርኩ፣ አወቅሁ ብለውም አልተኩራሩም፤ የተማሩትን ትህትና እና ምግባርን ተገበሩት እንጂ፡፡ አሁን ላይ ከልጅነት እስከ እውቀት የተማሩትን ፍቂህ እና ሀዲስ በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡
የአሁኑ ትውልድም ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ ሥነ ምግባር ተምሮ ማደግ አለበት የሚሉት ሐጂ በየጊዜው እና በየቦታው የሚሰማው ግጭት እና ሁከት በሥነ ምግባር ያልታነጸ ትውልድ ውጤት መኾኑንም ነው የጠቆሙት፡፡ የሃይማኖታዊም ኾነ ዘመናዊ ትምህርት ተማሪዎች ሥነ ምግባር ከሌላቸው ለሀገርም ለሃይማኖታቸውም እንደማያገለግሉ ይገልጻሉ።
በወጣትነት ጊዜያችን ከጓደኞቻችን ጋር በመከባበር እና በመተዛዘን ነው ያደግነው፡፡ ለዚያም ነው በኛ ዘመን የከፋ መጠላላት እና በነፍስ መፈላለግ ያልነበረው ይላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው አንዱ ሌላውን ማዋረድ እና መሳደብ፣ መዘራረፍ እና ማንቋሸሽ የሚመነጨውም ወጣቶች በሥነ ምግባር ታንጸው ያለማደግ ውጤት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የእስልምናም ኾነ ክርስትና ሃይማኖቶች መከባበርን እንደሚሰብኩ ጠቅሰው በአሁኑ ጊዜ ፍላጎትን ከሥራ፣ እና ከጸሎት ይልቅ በጉልበት ለማግኘት የመሞከር ችግሮች እንዳሉ ነው የጠቀሱት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ስለማይጠቅም እንደ ድሮው መሰማማቱ እና መከባበሩ ነው የሚበጀን ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥነ ምግባር መኮነን አቶ ጉባኤ ካህሌው መልካም ሥነ ምግባር የጠፋበት ምክንያት በዓለማችን የጦር መሣሪያ እና የቴክኖሎጂ እንጂ የጥሩ ሥነ ምግባር እሽቅድድም ባለመኖሩ ነው ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያም ሥነ ምግባርን የተላበሰ ትውልድ ለመፍጠር ሙከራው ቢኖርም ውጤታማ እንዳልኾነ ነው የገለጹት፡፡
በየጊዜው እና በየቦታው የሚስተዋሉ አላግባብ ለመጠቀም መፈለግ፣ ፍላጎቶቹ ካልተሳኩ በማኅበረሰብ እና ሀገር ላይ አደጋን መፍጠር የትውልዱ በሥነ ምግባር አለመቀረጽ ውጤቶች መኾናቸውን አብዛኛውን ሰው የሚያስማማ ነው፡፡ የሃይማኖት እና የባህል ተቋማት ለሥነ ምግባር እሴቶችን የሚሰጡት ዋጋ አሁንም ድረስ አለመክሰሙን፤ ነገር ግን በትምህርት ቤቶች በዴሞክራሲያዊነት ሽፋን ተማሪዎች ሲያጠፉ የማይቀጡበት፣ በቂ እውቀት ሳይዙ ከክፍል ክፍል የሚዛወሩበት ልማድ መኖሩ ለሥነ ምግባር መበላሸት ምክንያት እንደኾነ ይነገራል፡፡ የትውልዱ ያልሠራበትን የማግኘት ፍላጎትም ከዚሁ የአስተዳደግ ጉድለት እንደሚመነጭ ይነገራል፡፡
አቶ ጉባኤ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፡፡ መምህራን ለተማሪዎቻቸው በሥነ ምግባር ተኮትኩተው ማደግ ቁርጠኛ ከኾኑ ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው መቅረጽ ይችላሉ ነው የሚሉት፡፡ ተቀባይነት ያለው መምህር ለተማሪዎች ለራሳቸው ሕይዎት የሚጠቅመውን ብቻ ሳይኾን ለግሉ ጥቅም እንኳን ሥሩ ቢላቸው ይተገብሩታል ነው ያሉት፡፡
መምህራን የሚያስተምሩትን እና የሚመክሩትን በመስማት መተግበሯ ለተሻለ ውጤት እንዳበቃት ተማሪ ሂትራም ትናገራለች። መምህሮቻቸው ጥሩ ስለኾኑ እና በተማሪዎችም ስለሚከበሩ ለተማሪዎች የሚጠቅመውን እንደሚመክሩ እና ተማሪዎችም እንደሚተገብሩት ነው የገለጸችው። ይልቁንም የላይኛው አካል ለታችኛው የሰጠውን ሥራ አለመከታተል እና አለመደገፉ ችግር እንደኾነ ነው የጠቀሱት፡፡ የሐሰት ሪፖርትም ሌላኛው ችግር ነው። በድምር ውጤቱ ለትውልድ ሥነ ምግባር ብልሽት እንደሚያጋልጥ ነው ያብራሩት፡፡
የሥነ ምግባር ብልሽትን ለመቀነስ ወጣቶች በእውቀት እና በሥነ ምግባር ተቀርጸው በሚያድጉባቸው ትምህርት ቤቶች የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ መተግበር መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡ የወጣቶች የሥነ ምግባር ቀረጻን በሕዝብ እና በመንግሥት እየከፋፈሉ ችግሮችን ከመገፋፋት እና ከመካሰስ ይልቅ ሁሉም የየድርሻቸውን መሥራት እንደሚስፈልጋቸው ነው የተናገሩት፡፡
ቤተሰብ ልጆቹን የመከታተል ኀላፊነት እንዳለበት የጠቀሱት አቶ ጉባኤ የሃይማኖት ተቋማት እና ሲቪክ ማኅበራትም ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል፡፡ የልጆች አዕምሮ በአካባቢያቸው በሚመለከቱት ስለሚቀረጽ የፍትሕ ተቋማት ሠራተኞችም በሥነ ምግባር በመሥራት ለትውልዱ አርዓያ ሊኾኑ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ለችግሮች ያለፈውን መውቀስ ብቻ ሳይኾን ዛሬስ ምን እየተሠራ ነው ብሎ መጠየቅም መለመድ እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎች ይመክራሉ፡፡ መንግሥትም የየትውልዱን ሥነ ምግባር ለማሻሻል ያወጣቸውን ሕጎች እና አሠራሮች መተግበራቸውን መከታተል እና መቆጣጠር አለበት፡፡ በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለሥነ ምግባር መሻሻል በትምህርት ቤቶች ለሚሠራው ሥራ የክትትል ስልት ተበጅቶለት፣ የሥነ ምግባር ጉዳይ ተወካዮች ተመድበው እየሠሩ ነው፡፡ በጀትም ተመድቦለት ትኩረት ሰጥተን እንሠራዋለን፡፡ ተማሪዎችን በጥሩ ሥነ ምግባር ለመቅረጽ የሚደረጉ ጥረቶችን እያበረታታን ተሞክሮውን ለማስፋት የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል አቶ ጉባኤ፡፡
አቶ ጉባኤ እንደ ተማሪ ሂትራ በእውቀትም በሥነ ምግባርም የተገነቡ ወጣቶችን ለማብዛት መምህራን፣ ወላጆች፣ መንግሥት እና ባለድርሻ አካላት መረባረብ እና መተባበር እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡ የትውልዱ መልካም ሥነ ምግባር በሂደት ተሸርሽሮ ለሕዝብ እና ለሀገር በሚተርፍ የሞራል ዝቅጠት ችግር ውስጥ እንገኛለን። ችግሩ ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥም አይደለም። ደረጃው ይለያይ እንጂ ራሱ ወጣቱ፣ ወላጅ፣ ትምህርት ቤቶች፣ መንግሥት እንዲሁም የሃይማኖት እና ሲቪክ ተቋማት ለጥፋቱ ድርሻ አላቸው። መፍትሄውም ሳይገፋፉ እና በቸልታ ሳያልፉ ተቀራርበው እና ተመካክረው መሥራት እንደኾነ ነው ባለሙያዎች የመከሩት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
