
ሰቆጣ: ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብር በ2014 ዓ.ም የጀመረ ሲኾን ዋነኛ ዓላማውም የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን ወደ ልማታዊ ባለጠግነት መለወጥ ነው። ይህ መርሐ ግብር ባለፋት ሁለት ዓመታትም በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
አቶ አዲሴ ካሴ የሴፍቲኔት እርዳታ ተጠቃሚ የነበሩ ሲኾኑ ቤተሰቦቻቸውን ለማሥተዳደር የሚሰጣቸው የስንዴ እህል ባለመብቃቱ ምክንያት የቀን ሥራ በመሥራት በሚያገኙት ገንዘብ ይተዳደሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። በልማታዊ ሴፍቲኔት ተደራጅተው ባገኙት ድጋፍም የሽመና ሙያን በመሠልጠን ዛሬ ላይ በሥራቸው አራት ባለሙያዎችን ቀጥረው ማሠራት እንደጀመሩ ነው የነገሩን።
መንግሥት ያመቻቸላቸውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም እና ጠንክረው በመሥራታቸው ከተረጅነት ወደ ባለጠግነት መቀየራቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ አቶ አዲሴ በቀጣይም የሽመና ሥራቸውን በማዘመን ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል። ሌላኛዋ የልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚ ወይዘሮ አጫዋች ተክሌ አቅመ ደካማ እናታቸውን እና ወንድማቸውን ለመደገፍ ሲሉ ብዙ ፈተናዎችን እንዳሳለፉ ገልጸዋል።
ከመንግሥት ያገኙትን ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም የእህል መካዝን በማዘጋጀት የተሻለ ገቢ እያገኙ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል። በቀጣይም ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ለመግዛት ዝግጅት ላይ እንደኾኑ የገለጹት ወይዘሮ አጫዋች “ድህነት የተጻፈልን ሳይኾን ራሳችን የምንጽፈው መጥፎ ታሪክ ነው፤ ጠንክረን ከሠራን ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል” ሲሉ ነው የተናገሩት።
የልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብር በአምስት የልማት ዘርፍ በሰቆጣ ከተማ የሚሠራ ሲኾን የገንዘብ ድጋፉም ከዓለም ባንክ እንደኾነ የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘሩ ጌታወይ ገልጸዋል። በልማታዊ ሴፍቲኔትም 564 አባወራዎችን በመለየት ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለመለወጥ የተሠራ ሲኾን ለእያንዳንዳቸው ከ33 ሺህ ብር በላይ የመነሻ በጀት ከዓለም ባንክ ድጋፍ እንዳገኙ አቶ ዘሩ ተናግረዋል።
ለመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያም ዓለም ባንክ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ኀላፊው በቀጣይም “የእርዳታ እህል ከመጠበቅ እህል የሚያመርት ግለሰብ” ለመፍጠር ዓላማ አድርገው እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል። ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብር በዋግ ኽምራ ካሉ ከተሞች ውስጥ በሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር እየተተገበረ ያለ መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ የከተሞች ጽዳት አሥተዳደር እና የአረንጓዴ ልማት ቡድን መሪ ሰይድ መሐመድ ገልጸዋል።
ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከ500 በላይ የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በአምስት የሙያ ዘርፎች ማለትም በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ፣ በከተማ ግብርና፣ በተፋሰስ ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ በማድረግ ውጤታማ ሥራ እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
