“ዘመኑ የደረሰበትን የሕክምና አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ለመስጠት የሕክምና ትምህርት ክፍሎችን መደገፍ ይገባል” ካሣሁን ተገኘ (ዶ.ር)

35

ጎንደር: ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ለ178ኛ ጊዜ የሚከበረው የአንስቴዥያ ቀን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ተከብሯል። አንስቴዥያ ከቀዶ ጥገና በፊት፣ በቀዶ ጥገና ጊዜና ከቀዶ ጥገና በኃላ ሕክምና ለሚሰጣቸው ሰዎች ሕመም እንዳይሰማቸውና ሕክምናው የተሳካ እንዲኾን የሚያገለግል የሕክምና ዘርፍ መኾኑን በጎንደር ዩኒቨርስቲ የአንስቴዥያ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሔኖስ እንየው ገልጸዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሣሁን ተገኘ የዩኒቨርሲቲው አንስቴዥያ ትምህርት ክፍል ጠንክሮ በመሥራት በመማር ማስተማሩ ብቻ ሳይሆን በሕክምናው ዘርፍም በርካታ ምሁራንን እና ባለሙያዎችን እያፈራ ነው ብለዋል። ትምህርት ክፍሉ ከ250 በላይ ምርምሮችን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባላቸው ጆርናሎች ማሳተሙን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል።

ዘመኑ የደረሰበትን የሕክምና አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ለመስጠት የሕክምና የትምህርት ክፍሎችን መደገፍ ይገባል፤ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ለአንስቴዥያ ትምህርት ክፍል ድጋፎችን ያደርጋል ብለዋል። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ14 ክፍሎች የአንስቴዥያ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሕክምናው በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑን የአንስቴዥያ ትምህርት ክፍል መምህርና የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር አሥተባባሪ ታደሠ በላይነህ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የአንስቴዥያ ተማሪ አክሊሉ በላይ እና ባምላክ ብርሃኑ ቀኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መታሰቡ የሙያውን ክብር ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ትምህርቱ ከፅንሰ ሃሳብ በተጨማሪ በተግባር ተደግፎ እየተሰጠ መሆኑን የጠቀሱት ተማሪዎቹ፣ ተመርቀው ሲወጡ ሙያውን ለማሳደግና ኅብረተሰቡን ለማገልገል እንደሚሠሩ አንስተዋል።

ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ እና የዐይን ቆብ ፀጉር መቀልበስ ቀዶ ሕክምና እንደሚሰጥ አስታወቀ።
Next article“ድህነት የተጻፈልን ሳይኾን ራሳችን የምንጽፈው መጥፎ ታሪክ ነው” የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚ