
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ፋሲል ክፍለ ከተማ ከብሎክ መሪዎች፣ የእድር እና ጀምያ አባላት ጋር የጎንደርን ሰላም በማስጠበቅ ዙሪያ የጋራ ውይይት እየተካሄደ ነው። የውይይቱ ተሳታፊዎች የጎንደር ከተማ ምክር ቤት ያወጣውን መመሪያ አስመልክቶ የትጥቅ አያያዝ እና ጉራማይሌ የኾነ የደንብ ልብስ አለባበስ ለብሎክ ሥራ አስቸጋሪ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
በምሽት የመንገድ መብራቶች የተበላሹ መኾናቸው፣ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ለብሎክ ሥራው እኩል የኾነ ተነሳሽነት አለመኖሩ እና ከመታወቂያ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ አንስተዋል። በውይይቱ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ተገኝተው የጎንደር ከተማ ምክር ቤት የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ያወጣውን መመሪያ ቁጥር 6/2017 በተመለከተ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ማድረግ እንዳስፈለገ ገልጸዋል።
ምክትል ከንቲባዋ እንዳሉት የብሎክ ጥበቃ ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ማኅበረሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ሕግ የሚያስከብሩ አካላትን እንዲገነባ በማድረግ ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነትን ማስጠበቅ ይቻላል ብለዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት በአማራ ክልል መንግሥት የተሻሻለው ከተሞችን እንደገና ማቋቋም፣ ማደራጃ እና ሥልጠና መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 245/2009፣ አንቀጽ 14/ ንዑስ አንቀጽ 2/ሀ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መመሪያውን እንዳወጣ ነው የተገለጸው።
መመሪያው በከተማ አሥተዳደሩ ባሉት በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ቀበሌዎች በተደራጁ የቀጣና ብሎኮች ተግባራዊ የሚደረግ ነው። በስድስቱም ክፍለ ከተሞች በተቋቋሙ የቀጣና ብሎኮች ተግባራዊ የሚደረገው መመሪያው በአንድ ቀጣና ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ አባላት ያሉት ኮሚቴ የሚዋቀር ሲኾን የሰላም ዘብ ኮሚቴው በየደረጃው ለሚገኙ የፀጥታ ምክር ቤቶች ተጠሪ ይኾናል።
ምክትል ከንቲባዋ ከፀጥታ ኀይሎች ዩኒፎርም ጋር ለተነሳው ጥያቄ ትክክል መኾኑን ጠቅሰው ወጥ የኾነ መለዮ እንዲኖር ይደረጋል ብለዋል፡፡ የብሎክ ጥበቃው ለሕገ ወጦች የሚመች ባለመኾኑ ኅብረተሰቡ በጋራ በመቆም በየቀጣናው በንቃት በመሳተፍ የየቀጣናውን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
በመድረኩ የተገኙት የፋሲል ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አለባቸው ጀምበር መመሪያው የወጣው ቀጣናዊ ሰላምን በማረጋገጥ ልማትን ለማስቀጠል በመኾኑ የብሎክ መሪዎች የአካባቢያቸውን ማኅበረሰብ በማስተባበር መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የፋሲል ክፍለ ከተማ አሥተዳደር ዘርፍ ኀላፊ ተስፉ ገብረስላሴ መመሪያውን አስመልክቶ ለተወያዮች ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በሪፖርታቸውም የጎንደር ከተማ ምክር ቤት የከተማውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ያወጣውን መመሪያ አስመልክቶ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን መግለጻቸውን ከማዕከላዊ ጎንደር ኮሙዩኒኪሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
