
ደሴ: ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕታዊ አባ መፍቀሬ ሰብዕ ሥርዓተ ቀብር የፊታችን ቅዳሜ በሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ እና በአቡነ እየሱስ ሞአ አንድነት ገዳም እንደሚከናወን የቀብር አሥፈፃሚ ኮሚቴው ገልጿል። በተለያዩ አድባራት በሃይማኖታዊ አስተምህሮ፣ አንድነትን በማስተማር እንዲሁም በብዝኀ ሕይዎት ጥበቃ ሥራ ያገለገሉት አባ መፍቀሬ ሰብዕ ኪዳነወልድ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደሴ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ ጠበብት ሲራክ መለሰ ገልጸዋል።
የባሕታዊ አባ መፍቀሬ ሰብዕ ሥርዓተ ቀብር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ጠብቆ እንዲከናወን የቀብር ሥነ-ሥርዓት አሥፈጻሚ ኮሚቴ መቋቋሙ ነው የተነገረው፡፡ የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ በደመቀ መልኩ እንዲከናወን ለማድረግ ኮሚቴው ሥራውን ማጠናቀቁን የገለጹት ደግሞ የኮሚቴው ሠብሣቢ ተፈሪ ከበደ ናቸው።
ኮሚቴው ዛሬ ከቀኑ 1100 ሰዓት ጀምሮ የቀብር ሥርዓታቸው እስከሚከናወንበት ጊዜ ድረስ በደሴ ደብረ መድሐኒት መድሐኔዓለም እና በደሴ ደብረ ቤቴል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የጸሎት፣ የስንብት እና የፍትሐት ፕሮግራም እንደሚኖር አቶ ተፈሪ ገልጸዋል። እስከ ቅዳሜ በሚከናወነው የሽኝት ፕሮግራም ላይ የሌሎች ዕምነት ተከታዮች እና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችም መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ነው ያብራሩት።
ሥርዓተ ቀብራቸው የፊታችን ቅዳሜ በሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ እና አቡነ እየሱስ ሞአ አንድነት ገዳም ከቀኑ 9:00 ሰዓት እንደሚከናወን የገለጹት ሠብሣቢው አማኙ በሚከናወኑ ፕሮግራሞች ላይ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ሽኝት እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል። አባ መፍቀሬ ሰብዕ በግሸን ደብረ ከርቤ እና በተለያዩ አድባራት ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተው በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
