
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡባዊ ሰሃራ የሚገኙ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ለማሳደግ የሚያስችላቸው የብድር አቅርቦት እየፈተናቸው መኾኑን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል። በቀጠናው የሚገኙ እና በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶች የፋይናንስ፣ የመሥሪያ ቦታ እና የቴክኖሎጂ ግብዓት በከፍተኛ ኹኔታ እየፈተናቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እንደ ዓለም አቀፉ የንግድ ማዕከል መረጃ ከ70 በመቶ በላይ የሚኾኑ ሴቶች በአፍሪካ የንግድ ሥራቸውን ለማጎልበት የሚያግዝ የፋይናንስ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ያስረዳል። ይህ ኹኔታ ደግሞ ሴቶች ኢ – መደበኛ በኾነ የፋይናንስ አማራጭ እንዲሄዱ እና የግል ቁጠባ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል ይላል።
ከእነዚህ ሴቶች መካከል የ36 ዓመቷ ጋናዊት የሥራ ፈጣሪ አውግስቲን ቱፎር ትገኛለች። ቱፎር የድንች ጥብስ አዘጋጅታ እና አሽጋ በመሸጥ ሥራ ላይ ተሰማርታላች። በሥራዋ ውጤታማ ብትኾንም የፋይናንስ አቅርቦት ባለማግኘት ግን እየተፈተነች መኾኗን ትናገራለች። ብድር ለማግኘት ከ150 ሺህ ብር በላይ መቆጠብ እና የብድር ጥያቄዋን የሚገመግሙ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ ።
ከምንም በላይ ደግሞ ከ36 በመቶ በላይ የሚኾነው የወለድ ምጣኔ ፈተና እና እንቅፋት እንደኾነባት ትገልጻለች ።ይህን የሴቶችን ችግር ለመቅረፍ የዓለም የምግብ ድርጅት እና ዓለም አቀፉ የንግድ ማዕከል በጋራ በመኾን ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ‘ኤዋት’ የተባለ ፕሮግራም ይፋ አድርገዋል። ፕሮግራሙ በሥልጠና፣ በምርት ማሻሻል፣ በሽያጭ እና በፋይናንስ በመደገፍ በአፍሪካ ነጻ አህጉራዊ የንግድ ቀጣና ላይ እንዲሳተፉ ያግዛል።
አስማ ቤጉም ሚርዛ የ61 ዓመት ናይጄሪያዊት ስትኾን በግብርና ዘርፍ ሥራ ፈጣሪ ናት። እሷም እንደ ሌሎች በብድር ወለድ እና ለብድር የሚኾን ማስያዣ በሚባሉ እንቅፋቶች የብድር አቅርቦት ለማግኘት ያልቻለች ሴት ናት። በሌጎስ የተሰጠውን የፕሮግራሙን ሥልጠና ወስዳለች፤ እናም የንግድ ዕቅዷን እንዴት በተሻለ መንገድ ማዘጋጀት እንደምትችል ትምህርትን ወስዳለች ።
ፕሮግራሙ ሥልጠና መስጠት ብቻ ሳይኾን በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ ከሚችሉ የፋይናንስ ተቋማት ጋርም አብሮ የሚሠራ መኾኑም ተገልጿል። በምግብ ድርጅቱ የሥርዓተ ጾታ ባለሙያ የኾኑት ክላራ ፓርክ ድርጅታቸው የፆታ እኩልነት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ እና ሴቶች ገበያ እንዲያገኙ ፣ የንግድ ሕጎችን ተከትለው እንዲሠሩ እና የፋይናንስ ዕድል እንዲያገኙ እንደሚያግዟቸው ተናግረዋል።
እንደ ኤዋት ዓይነት ፕሮግራሞች ለአውግስቲን እና አስማ ያለባቸውን መዋቅራዊ እንቅፋት ለመቅረፍ የሚያስችል እውቀት እና ክህሎት እያበረከተላቸው እና የግብርና ሥራቸውን እንዲያሳድጉ እንደሚያግዛቸውም የአፍሪካ ኒውስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!