
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ)አፍሪካ በዓለም አቀፋዊ መድረኮች እና በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ተዋናይ እንድትኾን አህጉራዊ ስትራቴጅካዊ ውይይት እና የጋራ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገልጸዋል። የአህጉሪቱ መሪዎች የፖሊሲ መናበብን በመፍጠር እና በጋራ ጉዳዮች በመስማማት አህጉራዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የማረጋገጥ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የመጀመሪያው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታ እና ሰላም!” በሚል መሪ መልዕክት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በጉባኤው የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “አሁናዊ የዓለም ሥርዓት እና በአፍሪካ ላይ ያለው ተፅዕኖ” በሚል ርዕስ የመወያያ ሃሳብ አቅርበዋል።
አፍሪካ ከዓለም ቀዳሚ የሥልጣኔ መሥራቾች አንዷ መኾኗን የጠቀሱት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አሁን ላይ ግን ወደ ኋላ ከቀሩ የዓለም ክፍሎች አንዷ መኾኗ ሊያስቆጭ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የአፍሪካን ትንሳዔ እውን በማድረግ በዓለም መድረክ ተገቢውን ቦታ እንዲኖራት እና ተፅዕኖ እንድትፈጥር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
አፍሪካውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው እና በዓለም ሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ትርጉም ያለው መፍትሔ ተኮር ውይይት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የአህጉሪቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ አብነታዊ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ አፍሪካ በዓለም ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ተዋናይ እንድትኾን ስትራቴጅካዊ ውይይቶች እና ውሳኔዎች ያስፈልጋሉም ብለዋል።
አሁን ላይ አህጉሪቱ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ግልጽ እና የተናበበ የመፍትሔ ማዕቀፍ አለመኖሩንም ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም የነበሩ የዓለም ሥርዓቶች ለአፍሪካ የማይመቹ እና ጉዳቶችን ያስከተሉ እንደነበሩ ጠቅሰው በድኅረ የዓለም ጦርነት በነበረው ሥርዓት ውስጥ የአፍሪካ እሳቤዎች ወደ ጎን ተብለው እንደ ነበር አውስተዋል።
ለረጅም ጊዜያት አፍሪካ የውጭ እርዳታ እና ብድር ጥገኛ ኾና መቀጠሏን በመጥቀስ ጥሬ የተፈጥሮ ሃብቷም ሲመዘበር መቆየቱን ጠቁመዋል። ከዚህም ባለፈ አፍሪካን የጦርነት ቀጣና በማድረግ ለብዙ ጉዳት እንደዳረጋትም አንስተዋል። ራስን ለመቻል ያለመ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ማንበር ላይም ውድቀቶች እንደነበሩ አውስተዋል።
የሉላዊነት መስፋፋትን ተከትሎ በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ አዳዲስ ኀይላት መምጣታቸውን ገልጸው ቻይና ሕንድ እና ሌሎችም የእስያ ሀገራት ሉላዊነትን ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር ሲጠቀሙበት በአንጻሩ አፍሪካ ወደ ኋላ መቅረቷን ተናግረዋል። አሁንም መሠረታዊ የዕይታ እና የስትራቴጅ ለውጥ ካልተደረገ አፍሪካ በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥም ተጎጅ ኾና የመቀጠል ስጋት እንደተደቀነባት ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ሀገራት አንድነታቸውን በማጠናከር አህጉራዊ ፍላጎት እና ጥቅምን ለማሳካት በአንድ እሳቤ፣ በአንድ ድምጽ እና በተባበረ ኀይል መሥራት አለባቸው ብለዋል። ለዚህም ስትራቴጅካዊ ውይይቶችን በማድረግ ወጥ ፖሊሲ ማዘጋጀት፣ በዓለም መድረክ በሚኖር ተገቢ ውክልና ላይ ተመሳሳይ አቋም መያዝ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ አህጉርን መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የአፍሪካን መፃዒ ሁኔታ በአዲስ መልክ ለመቅረጽ እና በዓለም አቀፋዊ መድረክ ጉልህ ሚና ለመጫወት ጊዜው አሁን ስለመኾኑ አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!