“ብዙዎችን የለወጠው ቅመማ ቅመም”

60

ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቅመማ ቅመም ብዙዎችን አርሶ አደሮች ወደ ባለሃብትነት ማማ አሸጋግሯል። ለሀገሪቱም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከፍተኛ ድርሻ አለው። ቅመማ ቅመም በአማራ ክልል በስፋት ከሚለማባቸው አከባቢዎች ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንዱ ነው፡፡
በ2016/17 የምርት ዘመን በዞኑ 38 ሺህ ሄክታር መሬት በቅመማ ቅመም ተሸፍኗል። በዚህም 50 ሺህ አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

ከአምራች አርሶ አደሮች አንዱ የኾኑት አርሶ አደር ጥበቡ እንግዳ እንዳሉት የቅመማ ቅመም ልማት ከጀመሩ ረጅም ጊዜ ቢያስቆጥሩም የግብርና ምክረ ሃሳቦችን ተከትለው ማምረት ከጀመሩ ግን ሦስት ዓመታትን አሥቆጥረዋል። በየዓመቱ ሁለት ሄክታር የሚጠጋ መሬት በርበሬ ያለማሉ። በአማካይ በሄክታር እስከ 30 ኩንታልም ያገኛሉ። በዚህ ዓመትም የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ የገለጹት አርሶ አደሩ አሁን ላይ ባለው ገበያ በኩንታል እስከ 32 ሺህ ብር ሊገኝ እንደሚችል ነግረውናል።

ከቅመማ ቅመም የሚገኘው ገቢ እያደገ በመምጣቱ በዚህ ዓመት ከበርበሬ ባለፈ አዝሙድ እና ሽንኩርት ማምረት ችለዋል። በቀጣይ በስፋት ለማምረት ማቀዳቸውንም ገልጸዋል። አርሶ አደሩ በቅመማ ቅምም ምርት ከሚገኝ ገቢ ቤተሰባቸውን ከመምራት ባለፈ በደልጊ ከተማ እስከ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቤት ሠርተዋል። ምርቱ ለአካባቢው አርሶ አደሮች አንዱ የአካባቢው መለያ መኾኑን ገልጸዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ ሀውልቱ ታደሰ እንዳሉት በዞኑ ከሚመረቱ ምርቶች አንዱ የቅመማ ቅመም ምርት ነው። የቅመማ ቅመም ልማት በዞኑ በሚገኙ 15 ወረዳዎች እየለማ ቢገኝም ምዕራብ እና ምሥራቅ ደምቢያ፣ ጣቁሳ እና ጎንደር ዙሪያ ወረዳዎች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

በ2016/17 የምርት ዘመንም 35 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ለማግኘት ታቅዶ እስከ አሁንም 38 ሺህ ሄክታር መሬት መሸፈን ተችሏል። 50 ሺህ አርሶ አደሮችም ተሳትፈዋል። በዞኑ በቅመማ ቅመም ከተሸፈነው ማሳ 14 ሺህ ሄክታሩ በበርበሬ የተሸፈነ ነው።

የጣቁሳ ወረዳ ደግሞ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። በወረዳው በሚገኙ 10 ቀበሌዎች በ100 ኩታ ገጠም 2 ሺህ 753 ሄክታር መሬት ሙሉ ፓኬጅ የተተገበረበት (ኮሚዲቲ ልማት) የኩታ ገጠም ልማት ማከናወን ተችሏል። 5 ሺህ 500 አርሶ አደሮች በልማት ሥራው ተሳትፈዋል።
በምርት ዘመኑ 437 ሄክታር መሬት በአራት ወረዳዎች በሚገኙ 27 ቀበሌዎች በ74 ኩታ ገጠም መሬት ነጭ ሽንኩርት መልማቱንም ነው የገለጹት።

በዞኑ ከሚመረቱት የቅመማ ቅመም ዓይነቶች ሌላኛው የነጭ እና ጥቁር አዝሙድ ነው። በምርት ዘመኑ በአራት ወረዳዎች ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተሸፍኗል። በዚህ ወቅትም በማልማት ላይ ይገኛል ብለዋል። በዞኑ የሚመረተው የአዝሙድ ምርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚመረተው ምርት 50 በመቶውን እንደሚሸፍን ገልጸዋል።

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ ከሚገኙ ምርቶች አንዱ መኾኑንም ነው የገለጹት። ሌላኛው በዞኑ ትኩረት የተሰጠው የቅመማ ቅመም ምርት ዝንጅብል ሲኾን በጭልጋ እና በጣቁሳ ወረዳዎች ከ200 ሄክታር በላይ መሬት ተሸፍኗል። በአጠቃላይ በዞኑ ከተሸፈነው የቅመማ ቅመም ምርት እስከ አሁን 60 በመቶ የሚኾነውን መሠብሠብ መቻሉን ቡድን መሪው ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ሁሉም ተማሪዎቻችን የዩኒቨርሲ መግቢያ ውጤት አስመዘገቡ።
Next articleበባሕርዳር በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 3 ሺህ ሊትር ነዳጅ ተያዘ።