
ደብረ ማርቆስ: ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2016 የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፍ ፈተናውን ከወሰዱ 33 ተማሪዎች መካከል 27 ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት አስመዝግበዋል። በተለያዩ አካባቢዎች በነበረው ግጭት ምክንያት በ2ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ፈተናውን የወሰዱት የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ሁሉም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል።
ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ነፃነት መልካሙ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት በኢትዮጵያ 3ኛ የሚያደርገውን 570 ውጤት አስመዝግቧል። ተማሪ ነፃነት ከነበረው አጭር የዝግጅት ጊዜ አንፃር ባመጣው ውጤት ደስተኛ መኾኑን ተናግሯል። ይህን ውጤት ለማስመዝገብ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙ እና የመምህራን አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ገልጿል።
እንደ ነፃነት ሁሉ ተማሪ ደሳለው ጋሻየ እና ተማሪ ራሄል ዳኛቸው 565 እና 450 ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። ተማሪዎች በጋራ በመኾን ለፈተናው በቂ ዝግጅት ማድረጋቸው ለዚህ ውጤት እንዳበቃቸውም ተናግረዋል። የተማሪዎቹ ቤተሰቦችም በተመዘገበው ውጤት መደሰታቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል። ወላጆች በትምህርት ቤቱ የሚሰጠው የመማር ማስተማር ሂደት ለተማሪዎች ምቹ መኾኑ ለዚህ ውጤት እንዳበቃቸውም ነው ያስገነዘቡት።
የአዳሪ ትምህርት ቤቱ የፊዚክስ መምህር ደባሱ አየነው ለተማሪዎች ውጤት መሳካት በውይይት ላይ ያተኮረ ትምህርት መሰጠቱ እና መምህራንም ሰፊ ጊዜያቸውን ለተማሪዎች መስጠታቸው ያመጣው እንደኾነ አብራርተዋል። የክብር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደረጀ ከፈለኝ በትምህርት ቤቱ ብዙ ያልተሟሉ ግብዓቶች ቢኖሩም ያሉትን የትምህር ግባቶች በአግባቡ ተማሪዎች እንዲጠቀሙ መደረጉ ለተማሪዎች ውጤት መሳካት አስተዋጽኦ ነበረው ነው ያሉት።
ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ውጤት የሚመዘገብበት ተቋም መኾኑን የገለጹት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ የዚህን ተቋም ውጤታማነት ለማስቀጠል ያሉበትን የመማሪያ ክፍል እጥረት እና ሌሎች ግባቶችን ለማሟላት እየተሠራ ነው ብለዋል። ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ በክልሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ከስምንተኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረም ይገኛል፡፡
በትምህርት ቤቱ በሁለተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ሁሉም ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ከፍተኛ ውጤት ስለማስመዝገባቸውም ነው የተገለጸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!