የኦፓል ማዕድን በሕግ እና መመሪያ ተቃኝቶ እንዲሠራ ተጠየቀ፡፡

75

ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2017ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለኢንዱስትሪ፣ ለጌጣጌጥ እና ለኮንስትራክሽን ሥራዎች የሚያገለግሉ የተለያዩ ማዕድናት ይገኛሉ፡፡ ሲሊካ ሳንድ፣ ጅፕሰም፣ ብረት፣ ኦፓል፣ ወርቅ እና ሌሎችም በክልሉ ከሚገኙ ማዕድናት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ማዕድናት መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጌጣጌጥ እና ለመዋቢያ ሥራ በመዋል የዓለምን ገበያ እየተቆጣጠረ ያለው ኦፓል ነው፡፡ ኦፓል በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በስፋት ይገኛል፡፡ በዞኑ የተለያዩ የማዕድን አይነቶች ቢኖሩም ኦፓል፣ ዚኦላይት እና ማንጋኔዝ የተባሉ ማዕድናትን ክልሉ በጥናት አረጋግጦ ያሳወቃቸው ናቸው፡፡

ኦፓል በጉባላፍቶ፣ በአንጎት፣ በጋዞ እና በመቄት ወረዳ በስፋት ይገኛል፡፡ በአንጎት ወረዳ 04 ቀበሌ ነዋሪው አቶ መለሰ ሆዴ በማኅበር በመደራጀት የኦፓል ማዕድን በማውጣት ሥራ ከተሰማሩ 12 ዓመት እንደኾናቸው ይናገራሉ፡፡ አቶ መለስ እንደሚሉት በራስ ተነሳሽነት ባሕላዊ በኾነ ዘዴ ማዕድን የማውጣት ሥራው አድካሚ ቢኾንም ኑሮን ለማሻሻል ሲባል ሥራውን እያከናኸኑ ነው፡፡

በሕገ ወጥ መንገድ ማዕድን የሚያወጡ ግለሰቦች ለሥራቸው ዋና እንቅፋቶች እንደኾኑባቸውም አቶ መለስ ይናገራሉ፡፡ የማዕድን ሃብቱ ሕጋዊ አደረጃጀት እና አሠራር ስላልተዘጋጀለት በወረዳው የተደራጁት የኦፓል አምራች ማኅበራት ሕጋዊ መሠረት ኑሯቸው ቢሠሩም በሕገ ወጥ መንገድ የተሰማሩት በቁጥርም ከፍተኛ በመኾናቸው በሥራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል፡፡ ለሀገር ጥቅም የሚውለው የማዕድን ሃብትም ብክነት እየደረሰበት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን የጋዞ ወረዳ የማዕድን ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቢክስ ተስፋው 26 በሚደርሱ ማኅበራት 261 አባላት ሕጋዊ በኾነ መንገድ ፈቃድ አውጥተው የማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ቁጥር ሦስት እጥፍ የሚኾኑት ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ የተሰማሩ ግለሰቦች እንደኾኑ አስረድተዋል፡፡

ይህ የከበረ ማዕድን ሕግ እና መመሪያ ተዘጋጅቶለት በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ሕገ ወጦች እንዲከብሩበት አለፍ ሲልም ለአካባቢው የፀጥታ ስጋት መንስኤ እንዲኾን በር ከፍቷል ነው ያሉት፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ አይደለም፣ በዚህም በወረዳው ሕገ ወጥነት እንዲበራከት እና ኦፓሉም እንዲባክን ኾኗል ነው ያሉት ኀላፊው፡፡

ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በተዋረድ ኀላፊነትን በመወጣት ሕገ ወጥ የማዕድን ማውጣት ሥራንም ኾነ ሕገ ወጥ ግብይቱ እንዲቆም መሠራት አለበት ሲሉም ጠይቀዋል። በሰሜን ወሎ ዞን ማዕድን ልማት መምሪያ የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ አሥተዳር ቡድን መሪ ሽፈራው በየነ ማዕድናቱ ሀገርን ወደ መጥቀም ደረጃ ለማምጣት ፈቃድ በመስጠት እና ወጣቶችን አደራጅቶ ሕጋዊ በኾነ መንገድ ለማሠራት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። በሕገ ወጥ መንገድ የተሰማሩት ማዕድን አውጪዎች እየተበራከቱ መሄዳቸውን ግን የዘርፉ ስጋት መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የኦፓል ማዕድኑ ከመጀመሪያም የክምችት መጠኑ ተጠንቶ እና ታውቆ መንግሥትም ዕውቅና ኖሮት በሕግ እና መመሪያ ተቃኝቶ አይደለም ማውጣት የተጀመረው ይላሉ ቡድን መሪው፡፡ በዚህም ምክንያት ዘርፉን ለሕገ ወጥ ተግባር የተመቸ አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሽፈራው አምራቹን ወጣት ተጠቃሚ አለማድረግ፣ በግብይቱ ላይ ሕገ ወጥነት መበራከት እና የአመራረት ሥርዓቱ ያልዘመነ መኾን ዋና ዋና የዘርፉ ችግሮች መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡

ሁሉም አካል ከኅብረተሰቡ እና ከጸጥታ አካሉ ጋር በመኾን ሕገ ወጥ አሠራርን ለማስቆም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረል፡፡ ከአመራረት እስከ ገበያ ትስስር ድረስ ያለው ሁኔታ ዘመናዊ አሠራርን የተከተለ እንዲኾን ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የማዕድን አወጣጡን በመሳሪያ በመታገዝ እና በማዘመን ከጉዳት የጸዳ በማድረግ ብሎም ሕገ ወጦችን በሕጋዊ መንገድ በማደራጀት የአካባቢውን ኅብረተሰብ፣ ክልሉን ብሎም ሀገርን ሊጠቅም የሚችል ሥራ መሥራት እንደሚገባም አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባህታዊ አባ መፍቀሬ ሰብዕ ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ።
Next articleየክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ሁሉም ተማሪዎቻችን የዩኒቨርሲ መግቢያ ውጤት አስመዘገቡ።