“የጤና ተቋማት ነጻነት መከበር፤ የባለሙያዎችም ደኅንነት መጠበቅ አለበት” ታፈረ መላኩ (ዶ.ር)

26

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የጤና አገልግሎቶችን እና የሰብዓዊ ድጋፎችን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱን ያዘገጀው በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ነው፡፡ የፎረሙ ጸሐፊ ታፈረ መላኩ (ዶ.ር) የጤና ተቋማት ነጻ ኾነው መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡

ሙያ እና ሙያተኛ እንዲከበር ሁሉም ተጽዕኖ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም በእውነት እና ስለእውነት በመቆም ለሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡ የታጠቁ ወገኖች የዓለም አቀፍ ሕጎችን፣ የጤና ተቋማትን ነጻነት እንዲያከብሩ፣ የባለሙያዎችን ደኅንነትን እንዲጠብቁ እና የሰብዓዊ ድጋፎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲደርሱ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሕጎች ክብር የምትሰጥ ሀገር መኾኗን ያስታወሱት ጸሐፊው ሕጎች እንዲተገበሩ እና እንዲከበሩ ሁሉም ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ ሕዝብ በግጭቱ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቁንም ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ እየደረሰበት ያለው ሰቆቃ ከፍተኛ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የጤና ተቋማት በምንም መመዘኛ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊኾኑን እንደማይገባም የፎረሙ ጸሐፊ ጠይቀዋል፡፡ ሕዝቡ ያለውን መልካም እሴት በመጠቀም ችግሮችን መፍታት እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ የጤና ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ኾኖ መሠራት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

የጤና ተቋማት ነጻነት እየተከበረ አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የጤና ባሙያዎች ደኅንነትን መጠበቅ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ሁሉም የጤና አገልግሎት በተገቢው መንገድ እንዲሰጥ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎርም በትብብር እንደሚሠራ ነው የተናገሩት፡፡

ሕዝባችን ለመደገፍ በችግር ውስጥም ኾነን መሥራት ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡ ሕዝብን ማገልገል እና ከችግር መታደግ የህሊና እረፍት እንደሚሰጥ እና ግዴታም መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጤና ተቋማትን ጠብቁልን” ፕሮፌሰር ፈንቴ አምባው
Next articleየብሪክስ ፕላስ የመረጃና እና የባህል ሚዲያ ማዕከል ተመሠረተ።