“የጤና ተቋማትን ጠብቁልን” ፕሮፌሰር ፈንቴ አምባው

12

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የጤና አገልግሎቶችን እና የሰብዓዊ ድጋፎችን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱን ያዘጋጀው በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ነው፡፡

የስትራቴጅክ ሰነዱን ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና መምህር እና ተማራማሪ እንዲሁም በኢትዮጵያ የማኀበረሰብ ጤና ማኅበር የአማራ ቻፕተር ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ፈንቴ አምባው “ሁሉም አካላትን የምንለምናቸው ዋጋ ከፍለውም ቢኾን የጤና ተቋማቱን እንዲጠብቁልን ነው” ብለዋል፡፡
“የጤና ተቋማትን ጠብቁልን፤ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን ማክበር ግድ ይላል፤ ሕጎችን አለማክበር ይውል ያድር ይኾናል እንጅ ተጠያቂ ያደርጋል” ነው ያሉት፡፡

የጤና ባለሙያዎች እየተፈናቀሉ፣ እናቶች እየሞቱ ነው፣ ለወገኖቻችን እንድረስላቸው ብለዋል፡፡ረጅም ጉዞ ጀምረናል የወገኖቻችን ችግር እስኪቀረፍ ድረስ በተከታታይነት መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል የጤና ሥርዓቱ በአግባቡ እንዳይሠራ ኾኗል ብለዋል፡፡ በክልሉ ተከታታይ የኾነ ግጭት በመኖሩ የጤና ተቋማት ተጎድተዋል፤ የጤና ባለሙያዎች መፈናቀል እና አለፍ ሲልም የሕይዎት መስዋዕትነት መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡

ከኮሮና ቫይረስ ጀምሮ ክልሉ በከፍተኛ የጤና ችግር ውስጥ መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡ የኮሮና ቫይረስ ያመሰቃቀለው የጤና ሥርዓት ሳይሻሻል የሰሜኑ ጦርነት በክልሉ የጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንም አስታውሰዋል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት የወደመው መልሶ ሳይቋቋም በአማራ ክልል ሁሉንም አካባቢ ያዳረሰው ግጭት ተፈጠረ ነው ያሉት፡፡

አሁን ባለው ችግር የጤና አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ መንገዶች ይዘጋሉ፣ ወገኖች ያለ ስጋት ወደ ጤና ተቋማት ሄደው መታከም አይችሉም ብለዋል፡፡የጤና አገልግሎቱ አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የሰብዓዊ አገልግሎት ድጋፍ ማድረስ፣ መልሶ ማቋቋም እና ማልማት ይገባልም ብለዋል፡፡

እኛ የምንሠራው ከየትኛውም ፖለቲካ ገለልተኛ ኾነን ነው፤ የጤና ሥርዓቱ ምንም ቢኾን ወደ ነበረበት መመለስ አለበት ነው ያሉት፡፡የታጠቁ ወገኖችን የምንለምናቸው የጤና አገልግሎቱን የሚጠብቁ ሕጎችን እንዲያከብሩ ነው ብለዋል፡፡ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ እና የሰብዓዊ አገልግሎትን እንዲጠብቁ እንለምናቸዋለን ነው ያሉት፡፡

የጤና ተቋማት ባለሙያዎች ገለልተኛ ኾነው እንዲሠሩም ጠይቀዋል፡፡ስትራቴጅው ውጤታማ እንዲኾን ሚዲያዎች በጎ ተጽዕኖ እንዲፈጥሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ሕጻናት እና እናቶች እንዳይሞቱ፣ መድኃኒት እንዲደርስ፣ በማንኛውም ሁኔታ መንገድ እንዳይዘጋ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ቀደም ሲል የተቆጣጠርናቸው ችግሮች አሁን በወረርሽኝ መልክ እየመጡ ነው፤ ቀድሞውንም ደካማ የነበረው የጤና ሥርዓት በእጅጉ እየተጎዳ ነው ብለዋል፡፡

ዓለም ካላገዘን ችግሩ እየከፋ እና እየሰፋ ይሄዳል ነው ያሉት፡፡ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለሙያዎች እየተፈናቀሉ እና የጤና ተቋማት አገልግሎት ለመስጠት እየተቸገሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል ለንፁሐን ወገኖች ለመድረስ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ካለው ሰፊ ችግር አንጻር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በቂ አይደሉም” ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ
Next article“የጤና ተቋማት ነጻነት መከበር፤ የባለሙያዎችም ደኅንነት መጠበቅ አለበት” ታፈረ መላኩ (ዶ.ር)