“ካለው ሰፊ ችግር አንጻር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በቂ አይደሉም” ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ

17

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የጤና አገልግሎቶችን እና የሰብዓዊ ድጋፎችን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱን ያዘጋጀው በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ነው፡፡ በአማራ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ዘርፎች ችግሮች መከሰታቸው በስፋት ተነስቷል፡፡ እናቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በከፋ ችግር ውስጥ እያሳለፉ ነው፡፡

ታመው መታከም የማይችሉ ወገኖች በርካቶች ናቸው፡፡ ስለ ምን ካሉ ሕሙማን በነጻነት ወደ ሕክምና ቦታ መሄድ አይችሉም፣ የጤና ባለሙያዎችም በነጻነት ሕክምና አይሰጡምና ነው፡፡ የመድኃኒት አቅርቦትም በተፈለገው ልክ አይደርስም፡፡ በክልሉ ልብን የሚሠብሩ ነገር ግን ብዙዎች ያላዩዋቸው እና ያልሰሟቸው ችግሮች ሞልተዋል፡፡

በውይይቱ የተገኙ ተሳታፊዎች ባለፉት ጊዜያት ከገጠሙ ችግሮች ባለመማር ለተለያዩ ችግሮች አሁንም እየተጋለጡ እንደኾነ ነው ያስረዱት፡፡ ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ አገልግሎት ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ የጤና ባለሙያዎች ያሉበትን ችግር በማሳወቅ ችግሩ ልጓም እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ስትራቴጅው ተግባራዊ መኾን አለበትም ብለዋል፡፡ በሰላም ጊዜ ሁሉም ለራሱ አይንስም፣ በችግር ውስጥም ኾኖ ማገልገል ሰብዓዊነት ነው፣ ሰብዓዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም በችግር ውስጥ ኾነው በቁርጠኝነት መሥራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ በጸጥታ ችግር ምክንያት የወባ በሽታ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየጨመረ ነው፤ ሌሎች በሽታዎችም ጉዳት እያደረሱ በመኾኑ ለወገን መድረስ ይገባል ብለዋል፡፡

መቋጫ ያላገኘው ግጭት ማኅበራዊ ቀውስ እየፈጠረ እናቶች በቤታቸው እንዲወልዱ እና ለሕልፈት እንዲዳረጉ እያደረገ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት፡፡ ድምጻቸው ያልተሰሙ ሕጻናት እና እናቶች ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል፤ ወገኖቻችን ችግር በርትቶባቸዋል፤ በዓለም አቀፍ ተቋማት የተደነገጉ የሰብዓዊ መብት ሕጎች እየተከበሩ አይደለም ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡን፣ ዪኒቨርሲቲዎችን እና ሌሎች ተቋማትን በማስተባበር በፍጥነት ወደ ታች መድረስ አለብን ነው ያሉት፡፡ የኮሮና ቫይረስ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና አሁን በክልሉ ያለው ጦርነት ዜጎች እንደ ሰው ማግኘት የሚገባቸውን እንዳያገኙ እያደረጋቸው ነው፤ ንጹሐን ዜጎችም እየተጎዱ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

ካለው ሰፊ ችግር አንጻር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በቂ አይደሉም ነው ያሉት፡፡ በአንድ በኩል የግብዓት አቅርቦት አለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተገኘውን ግብዓት ማድረስ እንቸገራለን ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ በ2016 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወገኖች የወባ ሕክምና ማግኘታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ይሄን ያደረጉት በችግር ውስጥ ኾነው የሠሩ የጤና ባለሙያዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በአዲሱ በጀት ዓመት ደግሞ ከሐምሌ መጀመሪያ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ 548 ሺህ 318 ዜጎች የወባ በሽታ ሕክምና ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በችግር ውስጥም ኾነው የጤና ባለሙያዎች ከፍተኛ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ እንደዚህ እየተሠራ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠርም ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ከተቋማት ጋር ኾነው እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፎረም የቀረበው ሰነድ ተግባራዊ እንዲኾን በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡ ሁሉም አካል ተረዳድቶ መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡ የጤና ሥርዓቱ በተገቢው መንገድ እንዲሠራ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡ የሰብዓዊ አገልግሎት በተገቢው መንገድ መሠጠት አለበትም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ።
Next article“የጤና ተቋማትን ጠብቁልን” ፕሮፌሰር ፈንቴ አምባው