የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከቀረቡለት ቅሬታዎች ውስጥ 88 በመቶ ምላሽ መስጠቱን አስታወቀ።

91

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የክልሉን ገቢ በማሳደግ የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወቅቱን የገበያ ዋጋ ታሳቢ ያደረገ እና ከምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው ጋር የሚጣጣም ፍትሐዊ የቀን ገቢ ግምት ጥናት በ2015 ዓ.ም መጨረሻ አድርጓል።

ቢሮው ያጠናውን የቀን ገቢ ግምት ተከትሎ በ2016 ዓ.ም በግብር ከፋዮች የቀረቡትን ቅሬታዎች በአሠራሩ መሠረት ምላሽ መስጠቱን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የደንበኞች አገልግሎት ባለሙያ አያልነህ እጅጉ ገልጸዋል። በዚህ በጀት ዓመትም ከሐምሌ 01/2016 እስከ ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም ቅሬታ ካቀረቡ 15 ሺህ 645 ግብር ከፋዮች ውስጥ 88 በመቶ ለሚኾኑት ምላሽ መሰጠቱን ነው የገለጹት።

ምላሽ ከተሰጠባቸው ውስጥ 60 በመቶው እንዲጸና የተደረገ ሲኾን 39 በመቶ ለሚኾኑ ግብር ከፋዮች ደግሞ ጥያቄያቸው ተገቢ ኾኖ በመገኘቱ እንዲስተካከልላቸው ተደርጓል ነው ያሉት። ለ37 ግብር ከፋዮች ደግሞ በመጨመር ውሳኔ ተሰጥቷል። 12 በመቶ የሚኾኑት ቅሬታ አቅራቢዎች ጥያቄያቸው በሂደት ላይ ይገኛል። በቅሬታ አቅራቢዎች የቀረበው የገንዘብ መጠን ከ380 ሚሊዮን 824 ሺህ ብር በላይ እንደሚኾንም ገልጸዋል።

በሦስተኛ ወገን ይግባኝ ካቀረቡት 6 ሺህ 298 ግብር ከፋዮች ውስጥ 2 ሺህ 367 ለሚኾኑት ምላሽ ተሰጥቷል። በዚህም ከ131 ሚሊዮን 531 ሺህ ብር በላይ የገንዘብ መጠን መቅረቡን ገልጸዋል። ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ፣ ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና ወልድያ ከተማ አሥተዳደር የቀረበላቸውን ቅሬታ ሙሉ በሙሉ ምላሽ የሰጡ ናቸው።

ባለሙያው እንዳሉት አንድ ግብር ከፋይ የግብር ውሳኔ በተሰጠው በ21 ቀናት ውስጥ ቅሬታ ማቅረብ አለበት። ቅሬታ አቅራቢው ከአቅም በላይ በኾነ ምክንያት በ21 ቀናት ውስጥ ማቅረብ ካልቻለ እና ጉዳዩ በተቋሙ ኀላፊዎች ከታመነበት በ10 ተጨማሪ ቀናት ውስጥ ቅሬታውን እንዲያቀርብ ይፈቀድለታል። ከዚህ ውጭ ከኾነ የግብር ውሳኔውን እንዳመነበት ተቆጥሮ ግብሩን እንዲከፍል ይደረጋል።

ቢሮውም ለሚቀርቡ ቅሬታዎች በትንንሽ ከተሞች በ45 ቀናት በትልልቅ ከተሞች ደግሞ በ90 ቀናት ውስጥ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል። ግብር ከፋዮች ቅሬታቸውን ያለምንም ክፍያ የሚያቀርቡ ይኾናል። ይሁን እንጅ ቢሮው በተሰጠው ውሳኔ ያልረካ ግብር ከፋይ በሦስተኛ ወገን ይግባኝ የሚጠይቅ ከኾነ ወለድ እና ቅጣቱን ሳይጨምር ከተወሰነው ግብር 50 በመቶ መክፈል ይጠበቅበታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው” የአፍሪካ ኅብረት
Next articleፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ።