“ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው” የአፍሪካ ኅብረት

41

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለሰላም እና መረጋጋት ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ መኾኑን የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል። የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ጸጥታና ሰላም” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ነው።

በጉባዔው የተገኙት በአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች እና የፀረ-ሽብር ዘርፍ ኀላፊ ባባቱንዴ ባዮሚ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለሰላም እና ፀጥታ መስፈን እያበረከተች የምትገኘው አስተዋጽዖ የሚደነቅ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት በአዲስ አበባ ያዘጋጀችው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔም የአሕጉሪቷን የተወሳሰቡ የፀጥታ ችግሮች በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ መኾኑን አንስተው ለኢትዮጵያ ምስጋና አቅርበዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1950ዎቹ ጀምሮ ከኮርያ ጀምሮ እስከ ሶማሊያ ድረስ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመሳተፍ ተልዕኮዋን በሚገባ በመወጣት ግንባር ቀደም ሀገር እንደሚያደርጋት ተናግረዋል። የአየር ንብረት ለውጥ፣ እየተባባሰ የመጣውን ግጭት፣ የታጣቂ ቡድኖችን መጨመር እና አሳሳቢውን የምግብ ዋስትና እጦት ምላሽ ለመስጠትም በአፍሪካ ሀገራት መካከል ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በዓለም ላይ የሚስተዋለው ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት የአፍሪካን ሉዓላዊ መረጋጋት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ያሉት ኀላፊው ለዚህም የአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከር የአሕጉሪቱን አቅም ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል። የአፍሪካ ኅብረትም ዓለም አቀፍ ትብብሩን በማጠናከር ለአሕጉሪቱ ሰላም እና መረጋጋት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መኾኑን አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔም የአፍሪካ ኅብረት በ2063 የጥይት ድምፅ ማስቆም አጀንዳ ተስፋ በማለምለም የአሕጉሪቷን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ወሳኝ መድረክ መኾኑን አብራርተዋል። በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተጀመረው የጉባዔ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች እና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

እንደ ኢዜአ የጉባዔው ተሳታፊዎች የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የኾኑ ወታደራዊ አታሼዎች፣ ወታደራዊ ተመራማሪዎችም የኢትዮጵያ የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማት የለውጥ እርምጃና የልማት ሥራዎች ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ለ2 ሚሊዮን 982 ሺህ ሕጻናት የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት መሰጠቱ ተገለጸ።
Next articleየአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከቀረቡለት ቅሬታዎች ውስጥ 88 በመቶ ምላሽ መስጠቱን አስታወቀ።